አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በቂርቆስ ክፍለከተማ አዲስ ምዕራፍ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው የ2014 ዓም ትምህርትን አስጀመሩ።
በትምህርት ቤቱ ከንቲባዋ እንዲሁም ሌሎች አመራሮች ተገኝተው የዘንድሮውን ዓመት ትምህርት አስጀምረዋል።
ኢትዮጵያ የእናንተን በሰላም ማደግ በእውቀት መታነጽ በጉጉት የምትጠብቅ እና ለዚህም ጥረት የምታደርግ ሀገር ናት ብለዋል ከንቲባዋ፡፡
ተማሪዎችም በአዲስ ምዕራፍ ትምህርታችሁን ተከታትላችሁ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይኖርባችኃል ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ መምህራን እና የትምህርት ዘርፍ አመራሮች ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በ2014 የትምህርት ዘመን ከ910ሺህ በላይ ተማሪዎች ምዝገባ ያካሄዱ ሲሆን÷ በዛሬው እለትም በይፋ ትምህርት መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ገልጸዋል።
በትምህርት ዘመኑም በከተማዋ ለሚገኙ ከ600ሺህ በላይ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች ምገባን ጨምሮ የትምህርት ግብዓት ቁሳቁስ መርሐግብር እንደሚከናወን ኃላፊው ተናግረዋል።
በዕለቱም ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ እና ሌሎች አመራሮች በጋራ በመሆን የትምህርት ቁሳቁስ ለተማሪዎች አስረክበዋል፡፡
የተማሪዎችን የምገባ መርሃግብርም በይፋ አስጀምረዋል መባሉን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!