አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)መንግሥት ከህዝቡ ጋር በጋራ በመሆን ለዓመታት ተንሰራፍቶ የኖረውን ሌብነትንና ብልሹ አሰራር አጥብቆ ሊዋጋ ይገባል ሲሉ የታሪክ ፀሐፊው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ተናገሩ።
ሙስናን እና ሌብነትን የመዋጋት ኃላፊነት በሚገባ መወጣትሀገርን በአዲስ የለውጥ ጎዳና እንድትራመድ ያስችላል ብለዋል፡፡
አዲስ የተመሰረተው መንግሥትም÷ እውን ሊያደርጋቸው ከሚገቡ የቅድሚያ ተግባራት ውስጥ ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮችን መዋጋት መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ሌብነት አስከፊነትና የሚያደርሳቸውን ጉዳቶች በአለፉት 27 ዓመታት ከነበረው ብልሹ አሰራር ገፈት ቀማሽ የነበረ በመሆኑ በድጋሜ ለሚፈጠር የአስተዳደር ችግር እና በደል የሚታገስበት ትከሻ የለውም ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፡፡
የአሸባሪው ህወሓት ውድቀት የመጣውም ስር በሰደደ ሌብነትና ብልሹ አሰራር መሆኑን ጠቁመው÷ህሊናው የነቃንና ለውጥን ያመጣ ሕብረተሰብን ዳግም ለሌብነትና ለብልሹ አሰራር መዳረግ ውድቀትን ያመጣል ብለዋል፡፡
አዳዲሶቹ አመራሮችም ይህንኑ ተገንዝበው ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮችን ሊታገሉ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡
በቡድንና በጥቅም እየተሳሰሩ የሀገርን ሀብትና ንብረት ማሸሽም ሆነ ለራስ ጥቅም ማዋል ከዚህ ወዲህ እንደማይቻል ከህወሓት አሸባሪ ቡድን መማር ይገባል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም÷ መንግሥትም በዚህ ተግባር ውስጥ ተሳትፈው በሚገኙት አመራሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ሀገሪቱን ከውድቀት ሊታደግ ይገባል ብለዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!