Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዳያስፖራው ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ 122 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በሁለት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል 122 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ አብርሃም÷ ዳያስፖራው ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገው ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ እስካሁን ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት አቶ ሃይሉ÷ ባለፉት ሐምሌና ነሐሴ ወራት ብቻ 122 ሚሊየን ብር ድጋፍ ከዳያስፖራው መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

ከዳያስፖራ አባላቱ መካከል አቶ ፍቃዱ ተረፈ÷ የውጭና የውስጥ ሃይሎች ኢትዮጵያ እንዳትለማ ጫና ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህንን እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ለሚሰሩ ሃይሎች ዕድል ባለመስጠት የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ በእውቀታቸውና በገንዘብ የሚያደርጉትን ድጋፍ ከምንጊዜውም በላይ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ኢትዮጵያ አለማየሁ በበኩላቸው÷ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ካለን ላይ በመቀነስ ድጋፍ በማሰባሰብ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለማሻገር እየሰራን ነዉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት፣ በልማትና በትውልድ ቀረጻ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት በመስከረም 2013 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን÷ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችን የያዘ ነው፡፡

የምክር ቤቱ አባላት “እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ የፍቅር ጉዞ” በሚል ከአዲሱ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛል፡፡

አባላቱ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም የለገሱ ሲሆን÷ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃ ጎብኝተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version