አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 1ሺህ 496ኛው የመውሊድ በዓል በቡሬ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በተለይም አሸባሪው የትህነግ ቡድን በፈጸመው ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን ማዕድ በማጋራት ተከብሯል።
የበዓሉ ታዳሚዎች የዘንድሮውን መውሊድ ስናከብር በተለየ መንገድ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የመውሊድ በዓል በቡሬ ከተማ በድምቀት መከበሩን የቡሬ ከተማ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የዞን ተወካይ አብዱ ደጉ ተናግረዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።
በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ባሻገር ከ10 በላይ ሰንጋዎችን እርድ በመፈጸም የተፈናቀሉ ወገኖችን ማዕድ በማጋራት መከበሩን ተናግረዋል።
በዓሉ ሲከበር ሰላም እንዲወርድ ዱዓ በማድረግና መንግሥት ለንጹሐን ዜጎች ከለላ እንዲሰጥ በመጠየቅ ነው ያሉት ደግሞ ሐጂ ሙሐመድ ንጉሴ ናቸው።
በሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን በአማራ ላይ የሚደርሰው ጅምላ ጭፍጨፋ አሳዛኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሐጂ ሙሐመድ÷ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር እነዚህን ወገኖች በማሰብ እና በመርዳት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
መንግሥት ፈጥኖ የንጹሐንን ግድያ እንዲያስቆምና ሰላም እንዲሰፍንም ጠይቀዋል።
በቡሬ በታሪካዊው ቲጃኔ መስጅድ መውሊድን ለማክበር ከጎንደር፣ ከቻግኒ ፣ ከምስራቅ ጎጃም እንዲሁም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሃይማኖቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!