Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፍትህ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያዎች መተግበራቸውን ማረጋገጥ አለባቸው – ፍትህ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትህ አካላት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተቀመጡ መመሪያዎችን በአግባቡ መተግበራቸውን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ ሕግን መሠረት በማድረግ በጥንቃቄ ሊሰሩ እንደሚገባም ተመላክቷል።
የፍትህ ሚኒስቴር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ የአስፈጻሚዎችን አቅም ለማጎልበት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው።
በፍትህ ሚኒስቴር የንቃተ-ሕግ ዐቃቤ ሕግ ዮሐንስ ግርማ እንደተናገሩት ፥ የፍትህ አካላት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተቀመጠውን መመሪያ በአግባቡ መተግበራቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት በሕገ መንግሥቱ ገደብ ያልተጣለባቸው መብቶች መኖራቸውን አስታውሰው ፥ ይህንን ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
“አንድ ሰው ግዴታ የቀበሌ መታወቂያ ብቻ ሊይዝ አይገባም” ያሉት አቶ ዮሐንስ መንጃ ፈቃድ፣ የግል ወይም የመንግሥት የመሥሪያ ቤት መታወቂያን ጨምሮ ማንኛውም ማንነትን የሚገልጽ ሰነድ ማቅረብ በቂ መሆኑን ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ ማለት ሁሉም ጉዳይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዋጁ ይሸፈናል ማለት አለመሆኑን ጠቅሰው፥ ፀጥታ አስከባሪዎች የትኛው ይሸፈናል? የትኛውስ አይሸፈንም? የሚለውን መለየት አለባቸው ብለዋል።
የሚኒስቴሩ የንቃተ-ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክተር እንዳልካቸው ወርቁ በበኩላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ በተለይም በአተገባበሩ ላይ ያለውን ብዥታ ለማጥራት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በተለይ ከፍተሻ ጋር በተያያዘ ቅሬታ እየተሰማ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዲፕሎማቶች በአዋጁ ወቅት ያላቸው መብት ምን ድረስ ነው? ለሚለውም ግንዛቤ እንደሚያስጨብጥ አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መንገሻ ሞላ በበኩላቸው በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአሳሪና ታሳሪ መንፈስ ሊያዝ አይገባም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version