Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠ/ ሚ ዐቢይ በግንባር ለመፋለም ማቅናታቸው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር የገቡትን ቃል በተግባር ያሳዩበት ነው – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አለማፍረስ የመጣን ጠላት በግንባር ለመፋለም ዛሬ ማቅናታቸው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር የገቡትን ቃል በተግባር ያሳዩበት የታሪክ ምዕራፍ ነው ሲሉ የፖለቲካ ዘርፍ ምሁራን ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን÷ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት የሚከፈል ዋጋ እንደመሆኑ ግንባር ሁላችንም እንገናኝ ብለዋል ።

ይህን ተከትሎ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካና የህግ ምሁራን እንዳሉት÷ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ አርአያ በመሆን ህዝቡ ለአገር መጽናት የሚያደርገውን ርብርብ በማሳደግ በግንባር ለሚዋደቀው ወታደር ከፍተኛ ወኔን የሚጨምር ነው፡፡

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዶክተር ደጉ አስረስ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ከየትም አይመጣም ላሉት ንግግራቸው ተግባሩን የገለጹበት የታሪክ ምእራፍን ገልጠዋል ፤ ይህም ኢትዮጵያን ለማዳን ያላቸውን ቆራጥ ውሳኔ ያሳያል ነው ያሉት።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ሱራፌል ጌታሁን÷ የኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ የራሱን ጥቅም ሊያስጠብቅ የቋመጠ አሸባሪን ድባቅ ለመምታት የተደረሰ ውሳኔ ነው ያሉ ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአድዋ ጦርነት አንስቶ ለአገር ይከፈል የነበረን የመሪዎች ፊት አውራሪነት ታሪክ ደግመውታል ፤ ይህም ሰራዊቱና ህዝቡ ለበለጠ ድል የሚያነቃቃ ነው ብለውታል ።

በዋነኛነትም ኢትዮጵያውያን ሊያውቁ የሚገባው ሀቅ አገር ሊያፈርስ ቆርጦ ከተነሳ አገርን ለጠላት አሳልፎ ሊሰጥ ካሰፈሰፈ ሀይል ጋር እየተጋፈጥን መሆኑን ዛሬም ማስተዋል አለባቸው ነው ያሉት ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔም ይህንን ሀቅ ገፍቶ የሚያሳይ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ የተናገሩት ምሁሩ ከራሳቸው ደህንነት በላይ አገራቸውን ያስቀደሙ መሪ መሆናቸውን ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለዓለም ያሳየ ሁነት ነው ብለዋል ።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር አቶ ሀይሉ ነጋ በበኩላቸው÷ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እኔስ ለአገሬ ምን አደረኩላት ጥያቄን እራሴን እንድጠይቅ ያደረገ ፤ ወደ ግንባር ለመዝመት ወኔ ሆኖኛል ነው ያሉት ።

አገርን ለማፍረስ የተቧደኑ እኩዮችን ድባቅ መምታት የሁሉንም መስዋዕትነት ይጠይቃል ያሉት ምሁሮቹ የፖለቲካ እና የህግ ምሁራኑ ህዝቡ የመሪውን አርአያነት ተከትሎ ወደ ጦር ግንባር አሁኑኑ መዝመት ደጀን ለመሆን ፈጥኖ ይወስን ብለዋል ።

በሀይለኢየሱስ መኮንን

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version