አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፅ/ቤት መርሃ ግብር ላይ የሐዋሳ ከተማ ወጣቶችና ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች #በቃ የሚለውን ንቅናቄ አንግበው በመሰለፍ የውጭ ሀገራት ጫና ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመትም ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ተናግረው ÷ አቅማቸው በፈቀደው ደረጃ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንደሚቆሙ ያላቸውን አቋም አሳይተዋል፡፡
ወጣት ቤተልሔም አያኖ እድሜዋ ቢፈቅድ የመዝመት ፍላጎት እንዳላት ገልጻ ÷ አባቷም በጦር ሜዳ ለእናት ሀገሩ እየተዋጋ እንደሚገኝና ከአባቷ ጋር ድል የመቀናጀት ትልቅ ፍላጎት እንዳላት ተናግራለች፡፡
በእንባና በወኔም ሆና “ ምዕራባዊያን ከምወዳት ሀገሬ ላይ እጃችሁን አንሱ” ብላለች፡፡
የጠቅላይ ሚኒስተሩ መዝመት ከፍተኛ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው የገለፁት ወጣት ኃይለ ኢየሱስ ታምራትና ወጣት ሳራ አብርሃም ÷ እነሱም በሚፈለግበት ጉዳይ ሁሉ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር መገኘት እንዳኮራቸው በመግለፅ ሁሌም ከጎናቸው ነን ብለዋል፡፡
ወጣቶቹ ÷ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚጥሩ የውጭ ኃይሎችም እጃቸውን እንዲያነሱ ለማሳወቅ በማሰብ በጠዋት ተሰባስበው መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ÷ ኢትዮጵያዊያን እያለን ሀገር አትፈርስም ፤ በሲዳማ የምትገኙ ወጣቶችም “በቃ”ን በመቀላቀል የኢትዮጵያን እውነት ማሳየት ይገባል ብለዋል፡፡
ሠልፈኞቹ ÷ እኔ እያለው ኢትዮጵያ አትደፈርም ! በቃ ሊባሉ ይገባል በሚል እየተካሄደ የሚገኘው ንቅናቄም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በብርሃኑ በጋሻው
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

