Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጦርነቱ ከህውሓት ቡድን ጋር ብቻ አይደለም – ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጦርነቱ ከህውሓት ቡድን ጋር ብቻ አለመሆኑን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ÷ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ውሳኔ ሀገርን ከነ ክብሯ የሚያስቀጥል በመሆኑ ሁሉም ሊከተለው ይገባል።

ልጀ ዳንኤል ጆቴ ለኢፕድ እንደገለጹት ÷ ዘመቻው ሀገር የማጽናትና “ኢትዮጵያ” የሚለውን የነፃነት እና የታሪክ ስምና ክብር የማቆየት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር በመነሳሳት ዘመቻውን ሊቀላቀሉት ይገባል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመቻውን መቀላቀላቸው የሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን መሪዎች ባህሪን እንደሚያንጸባርቅ የጠቆሙት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ÷ ጀግኖች አባቶች ኢትዮጵያ የሚለውን የነፃነት ስም ያኖሩት ጠላትን በግንባር ተዋግተው መሆኑን አስታውሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውሳኔ የፕሮፖጋንዳ ጦረኞችን ከመዋጋት አልፎ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ሀገር ከነክብሯ እንድትቀጥል የሚያስችል ሥራ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ሁሉም ሊከተላቸው እንደሚገባም አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር ፍቅርና ወኔ ይዘው በመነሳታቸው ኢትዮጵያን ለመበታተንና ለመከፋፈል ከጫፍ አድርሰዋት የነበረችውን ሀገር መታደጋቸውንም አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ “ኢትዮጵያን ዘምቼ አድናታለሁ” በማለት ዘምተዋል፤ ሀገርን ለመታደግ የሕዝብ አደራ መወጣት አንዱ ኃላፊነት መሆኑን ማሳየታቸውንም አስመስክረዋል ብለዋል ልጅ ዳንኤል ጆቴ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ያደረጉት ዘመቻ ኢትዮጵያን ለማሳነስ በብሔር፣ በሃይማኖት በመከፋፈል የኖረው የትህነግ አሸባሪ ቡድንን ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ የአመራሩም ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ መላ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር የቀሰቀሰ የተግባር ዘመቻ ነው።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቁርጠኛ መሪ እንዳለው በተግባርም ጭምር ያዩበትና የመሰከሩበት መሆኑንም ጠቁመው ÷ የአባቶች የጀግንነት ስሜትና ወኔ በውስጣቸው መኖሩን እንደሚያሳይም ገልጸዋል።

አሸባሪው ትህነግ ለ30 ዓመታት የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ከሕዝቡ እንዲወጣ ሲያደርግ እንደነበር ገልጸዋል።

ከዓመት በፊትም የሀገር ደጀን በሆነው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው አስነዋሪ ተግባር አልበቃ ብሎት፤ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የማጥፋት ተግባሩን እንደቀጠለበት ጠቁመዋል።

ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሰለፍ በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት በመክፈት መጠነ ሰፊ የሰብዓዊና የቁሳዊ ውድመት ማድረሱን አስታውሰዋል።

ጠላትን በመፋለምም መምራትና መተግበርን ለማሳየት ውሳኔያቸው ወድቄና ተዋድቄ ‹‹ኢትዮጵያን›› አድናታለሁ የሚል የተግባር ሰው መሆናቸውን እንደሚያሳይም ተናግረዋል።

ጦርነቱ ከህውሓት አሸባሪ ቡድን ጋር ብቻ አይደለም ብለዋል።

ድሮ በጀግኖች አባቶቻችን ያላሳኩትን ወረራና ጭቆና በዚህ ዘመን ለማሳካት የሚያደርጉት ጦርነት መሆኑን ጠቁመዋል።

ትግሉ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካንም ከእጅ አዙር ጭቆና ነፃ የማውጣት ዘመቻ መሆኑንም ተናግረዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version