አዲስ አበባ ፣ ህዳር 15 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አገርና ታሪክን ሊያጠፋ የመጣውን ወራሪ ሃይልን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የቆረጡ የሚሊሻና የፋኖ አባላት የአገር የመከላከያ ሰራዊት አባላትን እንዲቀላቀሉ በደብረብርሃን ከተማ ዛሬ ሽኝት ተደረገላቸው።
ያነጋገርናቸው ሽኝት የተደረገላቸው የሚሊሻና የፋኖ አባላት አገር ለማፍረስ ታሪክና ማንነትን ሊያጠፋ የመጣውን ጠላት ሳናንበረክክ አንመለስም ሲሉ በጀግንነት ወኔ እልህ በተናነቀው ስሜት ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በግንባር እንገናኝ ጥሪ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው የነገሩን አባላቱ ጤናማ የሆነ ብቻ ሳይሆን ህይወት ያለው ሁሉ ለራሱና ለአገር ህልውና እራሱን አሳልፎ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
አርዓያ ከሆኗቸው ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ጎን መሆናቸውን ያረጋገጡ የአማራ ክልል አመራሮችም በግንባር የሚሰለፉ ፋኖና ሚሊሻዎችን ይዘው ዘምተዋል።
በወሎ እና በሸዋ ያለውን የጦር ግንባር ሲያስተባብሩ ያገኘናቸው የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኅላፊ አቶ ፍቅረማርያም ደጀኔ ዘመቻውን የሚቀላቀሉ ፋኖዎችና ሚሊሻዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም በሚችለው አሸባሪውን በመደምሰስ ታሪክን ማደስ አገርን ከውርደት የመታደግ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።
ሌላው የክልሉ አመራር ሆነው በግንባር እያስተባበሩ ያሉት አቶ መስፍን አበጀ አቅም ያለው በጦር ግንባር ያልቻለ ደግሞ በስንቅ ዝግጅትና ማቀበል ከመከላከያ ጎን መሆኑን ማረጋገጥ አለበት ነው ያሉት።
በታለ ማሞ