Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከአሸባሪው ሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው 33 ሰዎች በይቅርታ ወደ ህዝቡ ተቀላቀሉ

 

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምዕራብ አርሲ ዞን ሄበን አርሲ ወረዳ ከአሸባሪው ሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው 33 ሰዎች ከ7 ቀበሌዎች በይቅርታ ወደ ህዝቡ ተቀላቀሉ።

ከአሸባሪ ቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው እነዚህ ሰዎች አሸባሪዎቹ ትህነግና ሸኔ ጋብቻ ፈፅመው በአገር ላይ ጦርነት መክፈታቸው ፍፁም ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ አጀንዳቸውም የጥፋት መሆኑን ተረድተን ወደ ህዝባችን ተመልሰናል ብለዋል።

ከህወሓት ጋር ጥምረት ተፈጥረው አገርን መውጋት በኢትዮጵያ ጀግኖች አጥንት ላይ መሄድ በመሆኑ ነው የጥፋት አጀንዳቸውን ተቃውመን ወደ ህዝባችን የተመለስነው ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጠላት መሆኑን በሚገባ ተረድተናል ከህዝባችን ጎን ቆመን የአገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል ።

የምዕራብ አርሲ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሃጂ÷ የኦሮሞን ህዝብ ትግል የተረዱ ወጣቶች የአሸባሪውን ቡድን የጥፋት አጀንዳ ተረድተው እየተመለሱ ይገኛሉ ብለዋል።

በጫካ ውስጥ የሚገኙትንም ለመመለስ ከአባ ገዳዎችና አገር ሽማግሌዎች ጋር የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለፁት።

የህዝባቸውን የሰላም ጥሪ ወደኋላ በመተው የጥፋት አጀንዳቸውን በሚያራምዱት ላይ እየተወሰደ ያለው ህግን የማስከበር ዘመቻም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የሄበን አርሲ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አወል ዋፎ እነዚህን ወጣቶች ከጥፋት አጀንዳቸው መመለስ የተቻለው ከህዝብ ጋር በቅንጅት በተሰራ ስራ ነው ያሉ ሲሆን ÷የወረዳው ህዝብ ሰላምን ለማስከበር የጀመረውን ትብብር እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በቢቂላ ቱፋ

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version