አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በርካታ የጦር መሳሪያዎች እና ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ ቁሳቁስ ተያዙ።
የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘካሪያ እንደገለፁት÷አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ በአገር ላይ የደቀኑትን አደጋ ለመከላከል በክልሉ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ የኮማንድ ፖስቱ ኮሚቴ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የተጠናከረ ስራ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
በዚህም ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎች እና ወታደራዊ አልባሳት ከተጠርጣሪዎች ጋር በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላዎችን ተላልፈው በተገኙ አካላት እና በተደረጉ ፍተሻዎች በርካታ የነብስ ወከፍ ሽጉጦችና ክላሾች ተይዘዋል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም በግለሰብ እጅ መገኘት የሌለባቸው የጦር ሜዳ መነፀሮችና ቴሌስኮፖች፣ የአሁኑ እና የቀደመው የአገር መከላከያ ሰራዊት አልባሳት፣ የፖሊስና ሚሊሻ አልባሳት፣ 830 ሲም ካርዶች፣ 10 ላፕቶፖች እና 107 ሞባይል ቀፎዎች መያዛቸውን ጠቁመዋል።
ከአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 467 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ለአሸባሪዎቹ የገንዘብ ምንጭነት ይውላሉ ተብለው የተጠረጠሩ ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ ሱቆች እንዲሁም 67 የባንክ አካውንቶች መታገዳቸውን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ሰርጎ ገቦችንና ፀረ ሰላም ሃይሎችን ከማጋለጥ እና አካባቢውን ነቅቶ ከመጠበቅ አንፃር እያከናወነ የሚገኘውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

