Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮ-ጂቡቲ መስመር የአሸባሪው የህወሓት ተላላኪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮ-ጂቡቲ ዋና መስመር የህወሓት የሽብር ቡድንን አገር የማፍረስ እኩይ አላማ ለማሳካት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ተላላኪዎች በቁጥጥር ስር በመዋል ላይ መሆናቸውን በሚሌ ጉምሩክና አካባቢው ለግዳጅ የተሰማሩ የመከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት አስታወቁ፡፡
ከአዲስ አበባ – አዋሽ – ሚሌ – ጋላፊ – ጂቡቲ የተዘረጋውንና የወጪና ገቢ ንግድ ዋና ኮሪደር የሆነውን የአስፓልት መንገድ ተቆጣጥሬያለሁ በሚል የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት የተጠመደው የህወሓት አሸባሪ ቡድን ሃሰተኛ መታወቂያዎችን በመያዝና የጦር መሳሪያዎችን በማስታጠቅ ለድብቅ ዓላማው ያሰማራቸው ተላላኪዎቹ ከተለያዩ የደንብ ልብሶችና ወታደራዊ መጠቀሚያዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች የተናገሩት፡፡
በፍተሻ ጣቢያው ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአፋር ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር በጥምረት በመሆን የተቀናጀና የተጠናከረ ፍተሻ በማድረግ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት የሰራዊቱ አመራሮች በቀጣይም በየትኛውም መልኩ የሽብርተኛው አገርን የማፍረስ ውጥን እውን እንዳይሆንና በዋናው መስመር የተለመደው የትራፊክ ፍሰት እንዲቀጥል ተግተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
በሚሌ ጉምሩክ ጣቢያ የሚሰሩ የፍተሻ ባለሙያዎችና በመስመሩ የሚመላለሱ የከባድና ቀላል መኪኖች አሽከርካሪዎች በበኩላቸው ÷ ማህበረሰቡ የሃሰት ወሬዎችን እየፈበረኩ ሀገር ለማፍረስ የሚታትሩ የጁንታው ቅልብ ልሳኖች የሚያሰራጯቸውን መረጃዎች ወደ ጎን በመተው የሀገሪቱን ህልውና ለማስጠበቅ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ካሉ የፀጥታ ኃይሎች ጎን እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version