ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሸባሪው ህወሃትን ወረራ ከፈፀመባቸው አካባቢዎች ለማፅዳት በጦር ግንባር በመሆን የወገንን ጥምር ኃይል በመምራት ላይ ይገኛሉ።
በዚህ የዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የወገን ጦር በሁሉም ግንባሮች በአሸባሪው ህወሓት የተያዙ አካባቢዎችን እያስለቀቀ አካባቢውን ከአሸባሪው ቡድን እያፀዳ ይገኛል።
በትናንትናው ዕለትም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት፣ በ”ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” ባካሄደው ኦፐሬሽን፣ የተለያዩ ከተሞችን ከአሸባሪው ሕወሃት ነጻ የማውጣቱንና በጥልቀት በመግባት የአሸባሪውን ጀሌዎች የመማረክና የመደምሰስ ተግባሩን መቀጠሉን ገልጿል።
በዚህም መሠረት በጋሸና ግንባር ቀውዝባና ጭላ ከተሞችና አካባቢያቸው ከአሸባሪው ኃይል ነጻ የወጡ ሲሆን፣ በወረኢሉ ግንባር በተደረገው ኦፐሬሽን ደግሞ አጅባር፣ ተንታ እና ዶባ ከተሞችና አካባቢያቸው ነጻ ወጥተዋል።
በተያያዘም በከሚሴ ግንባር ማጀቴን፣ ጭረቲን፣ ከሚሴን፣ ርቄን፣ ወለዲን፣ አልቡኮ ከተሞችን እና የቃሉ ወረዳን አብዛኛውን ክፍል በመቆጣጠር፣ ጥምር ጦሩ ወደ ኢንዱስትሪ ከተማዋ ኮምቦልቻ እየገሠገሠ ይገኛል።
ትናንትና ከትናንት ወዲያ በተደረጉት ከፍተኛ የማጥቃት ኦፐሬሽኖች አብዛኛው የአሸባሪው ኃይል ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲበተን ተደርጓል።
ጥምር ጦሩ በጥልቀት በመግባት የተበተነውን አሸባሪ በመልቀም ላይ ሲሆን አብዛኞቹ ጀሌዎች ሲደመሰሱ ቀሪዎቹ እጅ በመስጠት ላይ ይገኛሉ ብሏል።