አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ ) ኢትዮጵያ ላጋጠማት ችግር መላውን መፈለግ የእኛ የኢትዮጵያውያን ድርሻ ነው አሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ።
16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በድሬዳዋ ከተማ ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በአገር ህልውና ላይ የመጣውን ፈተና ሁሉም ዜጋ ችላ ማለት እንደሌለበት አንስተዋል።
ሀገር ለማፍረስ እና አንድነትን ለመናድ የተደረገው ሙከራ ቀይ መስመር ያለፈ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይሄንን ክህደት እና ወንበዴነት የትኛውም መንግስት ቁጭ ብሎ ሊመለከተው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
ሀገር አደጋ ላይ ስትወድቅ ዜጎች ከዳር እስከ ዳር ያደረጉት ርብርብ ደግሞ ጽኑ መሰረት ላይ መሆናችንን አሳይቶናል፤ ተገደን ለገባንበት ጦርነት ጥሩ ደጀን መኖሩን ተረድተናልም ነው ያሉት፡፡
ይህም በሀገር ቤት ብቻ የተወሰነ አለመሆኑን ገልጸው፥ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ከሀገር ውስጥና ከውጭ የመጣብንን ጥቃት ለመከላከል ለሚወስዱት እርምጃና ላንፀባረቁት የአንድነት ስሜት፣ ደጀንነት እና ወገንን በመደገፍ ላሳዩት ችሮታ አመስግነዋል፡፡
ዳያስፖራዎች ድርጊታችሁ እና የአገር ተቆርቋሪነታችሁ ሁላችንንም አርክቶናል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ የተሳሳተና ያልተጣራ መረጃ ምንኛ እንደጎዳን አይተናልም ብለዋል፡፡
በውስጥ እና በውጭ የተከፈተብንን ፈተና አንድ ከሆንን አሁን እንዳየነው እንወጣዋልን፣ ኢትዮጵያ ከሁላችንም በላይ ናት፣ እንጠብቃት፣ እንከባከባት፣ ሀገር አፍራሽን በጽኑ ሁላችንም መታገል ይኖርብናል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
17ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን እንዲያዘጋጅ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን በመምረጥ÷በድሬዳዋ ስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 16ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ተጠናቋል፡፡
በየሻምበል ምህረት
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

