አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ቡድኑ ህወሓት በኮምቦልቻ ከተማ ከሚገኙ ፋብሪካዎች ምርቶችንና ግብዓቶችን መዝረፉ ተገለፀ፡፡
የጋዜጠኞች ቡድን በኮምቦልቻ ከተማ በሽብር ቡድኑ የወደሙና የተዘረፉ ፋብሪካዎችን ጎብኝቷል።
በኮምቦልቻ ከተማ 200 የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት አልሚዎች ሀብታቸውን ማፍሰሳቸው ተገልጿል፡፡
ከእነዚህ ውስጥም 37 የሚሆኑት ፋብሪካዎች ምርት ማምረትና ወደ ውጭ መላክ መጀመራቸውን የከተማው የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ሃላፊ አቶ አባይነህ አበበ ተናግረዋል፡፡
ሃላፊ እንዳብራሩት የሽብር ቡድኑ በአብዛኞቹ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚገኙ ምርቶችና ግብዓቶችን ዘርፏል፡፡
መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪ ማሽኖችን በመነቃቀልና በማበላሸት መስራት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።
አብዛኞቹ አምራቾች ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ የሚልኩ ሲሆን ለሀገር የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ተቋማት መሆናቸውንም ተናግረዋል ሃላፊው፡፡
እነዚህ ፋብሪካዎች ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ እንደነበሩ እና አሁን ላይም እነዚህ ዜጎች ለችግር መጋለጣቸውን ነው የገለጹት፡፡
በማሽኖቻቸው ላይ ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው ፋብሪካዎች መካከል፥ ኢቲ ዉድ የችቡድ ፋብሪካ፣አማር ፒፒ የከረጢት ፋብሪካ ፣ ዋሊያ የቆርኪ ፋብሪካና የአማራ ደን ልማት ማህበር ይገኙበታል።
የኮምቦልቻ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ የሱፍ፥ የሽብር ቡድኑ ህወሓት የውጭ ባለሀብቶችን ፋብሪካ ትኩረት አድርጎ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካዎቹን መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት የጉዳት መጠናቸውን የከተማው አስተዳደር እያጣራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ባለሃብቶቹም ፋብሪካዎቻቸው ግብዓቶችን ከውጭ እንደሚስገቡ የገለጹ ሲሆን፥ መንግስት የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ እንዲያደርግና የባንክ ብድር ላለባቸው ፋብሪካዎችም ባንኮች የእፎይታ ጊዜ ሊሰጧቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ የመብራትና የውሃ አገልግሎት በፍጥነት እንደተጀመረ ያስታወሱት ሃላፊው፥ ሌሎች ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶች እንዲቀረፉም ጠይቀዋል፡፡
በፈቲያ አብደላ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

