Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፖለቲካ አጀንዳን የያዙ የውጭ ጫናዎች አሁንም ኢትዮጵያ ላይ መቀጠላቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 5፣ 2014(ኤፍ ቢሲ) ከኋላቸው ሌላ የፖለቲካ አጀንዳን የያዙ የውጭ ጫናዎች አሁንም ኢትዮጵያ ላይ እየጨመሩ መምጣታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ሳምንታዊ መግለጫቸውን ሰጥተዋል።
በዚህ መግለጫቸውም አንዳንድ የውጭ ሀገራት ቀደም ሲል በሰላም ሀገር ዜጎቻቸው ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ሲያደርጉት የነበረው ውትወታ ሲከሽፍ በሌላ አቅጣጫ ጫና ለመፍጠር እየሞከሩ መሆኑን ነው ያነሱት።
ከዚህ ውስጥም አንዱ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ የተመረጠችባቸው ዓለም አቀፍ ጉባኤ የመካሄጃ ቦታ ከአዲስ አበባ እንዲሰረዝ ሌሎች ሀገራትን እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ማግባባት መጀመራቸው አዲሱ አካሄዳቸው ነው ብለዋል።
አንዳንዶች በፈረንጆቹ ሰኔ ወር አዲስ አበባ የምታስተናግደው የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት ጉባኤ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወር ከጀርባ እየወተወቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
እነዚሁ ወገኖች በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት ማለትም በ2022 በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ሌላ ሀገር እንዲያስተናግደው የቻሉበት ቦታ ሁሉ በመሄድ ለማግባባት እየሞከሩ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትን አንዳንድ ሀገራት ኢትዮጵያን በተመለከተ የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ እየተጠቀሙበት መሆኑንም አምባሳደር ዲና አንስተዋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ትናንት ባወጣው መግለጫም ይህ ሁኔታ እጅግ እንዳሳዘነው መግለፁንም ነው ያመለከቱት።
የምክር ቤቱ አባል ሀገራትም ይህንን የተወሰኑ ሀገራትን የፖለቲካ ፍላጎት ያነገበን የምክር ቤቱን እንቅስቃሴ በጥብቅ እንዲቃወሙም ኢትዮጵያ መጠየቋን አስታውቀዋል።
Exit mobile version