ትናንት የተካሄደውን የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባን ውሳኔ ኢትዮጵያ አትቀበልም ፤ ለተፈጻሚነቱም አትተባበርም – መንግስት
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ትናንት የተካሄደውን የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባን ውሳኔ ኢትዮጵያ እንደማትቀበልና ለተፈጻሚነቱም እንደማትተባበር መንግስት ገለጸ፡፡
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ ረፋድ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም የአንዳንድ አገራትን የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ መካሄዱን ኢትዮጵያ አጥብቃ እንደምትቃወም አመልክተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም ኢትዮጵያ ጠንካራ እና ገለልተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ተቋም መገንባቷን ገልጸዋል፡፡
መንግስት ለዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር ትልቅ ተነሳሽነት እንዳለውም አንስተዋል፡፡
ሆኖም የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማቀንቀን የሚፈልጉ አካላት ዳግም ጉዳዩን ለማንሳት መሞከራቸውን ገልጸው ÷ አጠቃላይ የሰብሰባው ሂደት ፖለቲካዊ አጀንዳ እንዳለው ማየት እንደሚቻል ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ያጠፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ሊታወቅ ይገባልም ነው ያሉት በመግለጫቸው፡፡
የሽብር ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች የፈጸመውን ግፍ ለመስማት ጆሮ የሌላቸው አካላት ያደረጉት ስብሰባ ቀድሞ ፍርድ ሰጥቶ ሸንጎ እንደመቀመጥ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት ለተመድ አብሮ ለመስራት እንደሚፈልግ ሲያሳይ የነበረው ተነሻስነት ላይ ውሃ እንደመቸለስ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ÷ የስብሰባውንም ውጤት መንግስት እንደማይቀበለው አስታውቀዋል፡፡
ትናንት የተደረገው ስብሰባም ኢትዮጵያ ማን በፈተናዋ ወቅት ከጎኗ እንዳለ የተመለከተችበት እንደሆነ አንስተው፥ ለወዳጅ አገራት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አክለውም በገለልተኛ እና ህጋዊ ሂደትን በጠበቀ መልኩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መካሄድ አለመካሄዱን ለመመርምር ለሚፈልጉ አካላት በሯ ክፍት ነውም ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ፖሊስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እና ህገ መንግስቱን በመጣስ ከአሸባሪዎች ጋር በመስራት ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ጋዜጠኞች ጋር በተያያዘ ሙያቸው ከለላ ሊሆናቸው አይችልም ሲሉ በማብራሪያቸው አንስተዋል ፡፡
በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ባለሙያዎቹ እንደማንኛውም ሰው ህግን ማክበር እንደሚገባቸው ግንዛቤ መውሰድ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

