አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከአምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው አካላት ገፊነት እና አስተባባሪነት የተላለፈው የተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ውሳኔ በኢትዮጵያ ምድር ተፈፃሚ አይሆንም ነው ያሉት፡፡
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የፖለቲካ ፍላጎትን መሠረት አድርጎ በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ኢትዮጵያ እንደማትቀበል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አግባብነት ካላቸው ተቋማት ጋር ትብብር ስታደርግ መቆየቷን አንስተዋል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር ተግባራዊ ማስተካከያዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እንዳላትም ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል የተመድ የሰብዓዊ መብት ተቋም እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባደረጉት የጋራ ምርመራ የተሰጡትን ምክረ ሀሳቦችን ለመተግበር ኢትየጵያ ተግባራዊ አንቅስቃሴ በማድረግ ላይ በምትገኝበት ጊዜ የተላለፈ ውሳኔ መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ የሽብር ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው የአማራ እና አፋር አካባቢዎች የፈጸማቸውን መጠነ ሰፊ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጥፋት በማውገዝ ምርመራ እንዲካሄድ ውሳኔ ቢያስተላልፍ ኖሮ ተገቢና የሚያስመሰግነው እንደነበርም ገልጸዋል።
የህወሓት ቡድን የእርዳታ አቅርቦት ለማስተጓጎል የሚወስደው የእብሪት ተግባርን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቸልታ መመልከቱን ጠቅሰው፤ በመንግስት በኩል ግን የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚቻለውን ሁሉ ማድረጉን አመልክተዋል።
መንግስት ለሰላም ሲባል የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ያስተላለፈ ቢሆንም የሽብር ቡድኑ ግን ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ያልነበረ መሆኑን አስታውሰው፥ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የመንግስትን ውሳኔ በአዎንታዊነት በመመልከት በአንጻሩ ደግሞ በህወሃት የእብሪት ተግባር እንዲገታ ጫና ባለማሳደሩ ችግሩን እንዳወሳሰበው ገልጸዋል።
የህወሓት በመንግስት የተወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ በአማራና አፋር የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ወረራ በመፈፀም በንጹሃን ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን፣ የመሰረተ ልማትና ሃይማኖታዊ ተቋማትን ማውደሙን፣ ህፃናትንና ሴቶችን መድፈሩ ገልጸዋል።
ይህም የህዝብ ቁጣን ቀስቅሶ በሰብዓዊ እርዳታ መስመሩን ለመዝጋት ያነሳሳበት ጊዜው እነደነበርም ነው ያስረዱት።
የህወሓት አሸባሪ ሃይል በደረሰበት ምት ይዟቸው የነበሩ አብዛኛው የአፋር እና የአማራ አካባቢዎችን በማስለቀቅ በመንግሥት የፀጥታ ሀይሎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ገልፀዋል። ይህም ቡድኑ “ለሰላም ሲል በወረራ ከያዝኳቸው አካባቢዎች ለቅቂያለሁ” ማለቱ ከተጨባጩ እውነታ ጋር የሚቃረን ስለመሆኑም አንስተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን መንግስት ቡድኑ በሚሸሽባቸው እያንዳንዱ የትግራይ መንደሮች እግር በእግር በመከተታል የመግባት ፍላጎት የሌለው መሆኑን ጠቁመው፥ ነገር ግን ቡድኑ መቸውም ቢሆን መልሶ ጥቃት የማድረስ አቅሙ የተዳከመ መሆኑ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አክለውም የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትን ማስጠበቅ የመንግስት ኃላፊነት እንደመሆኑ መጠን ትግራይን ጨምሮ በማንኛውም ሀገሪቱ አካባቢዎች ሰራዊቱን የማስፈር መብት እንዳለው መጠቆማቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በቀጣይም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለመ ሁሉን አካታች ውይይት እንዲኖር ማንኛውም በአገሪቱ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል አካል የሚሳተፍበት የህገ መንግስት ማሻሻያን ጨምሮ በሀገሪቱ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮችን የተመለከቱ ጉዳዮች ለውይይት ክፍት እንደሚደረጉም ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ሁሉን አቀፍ ውይይትንና ድርድርን አደበላልቀውት ሲቸገሩ ይታያል ያሉት አምባሳደር ሬድዋን÷ውይይቱ ከዓመት በፊትም የነበረና አሁን ግን ራሱን በቻለ ኮሚሽን ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ ጉዳዩ ስለ ህወሓት ወይም ሸኔ አይደለም፤ ይህኛው የራሱ ሌላ መልክ አለው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

