አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በችግር ውስጥ ለሚገኙ ህጻናትና ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋዊያን የገናን በዓል አስመልክቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የማእድ ማጋራት መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡
የማእድ ማጋራት መርሐ ግብሩን ያዘጋጁት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ነው፡፡
በመርሃ ግብሩም ከ300 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትም የክብር አረጋዊያን፣ አርበኞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ በችግር ውስጥ የሚገኙ ህጻናት መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡
በእለቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ህጻናትና ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋዊያን የገናን በዓል አስመልክቶ የመልካም በዓል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የማእድ ማጋራት መርሐ ግብሩን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ በጋራ በመሆን አስጀምረዋል፡፡
በዓሉን በማስመለከት ከአባትና ከእናት አርበኞች ተወካዮች የምስጋናና የምርቃት ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የማህበራት አመራሮች ፥ በምገባ መርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸዉ አረጋዊያን፣ ሴቶች፣ ህጻናትና በማዕከላት የሚገኙ ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ህዝቡም ይህን ዓላማ ተቀብሎ ባለዉ አቅም ሁሉ ይህንን የበዓል አጋጣሚ በመጠቀም በአቅራቢያም ሆነ ከሰፈር ርቀዉ የሚኖሩ ድጋፍና እንክብካቤ የሚሹ ወገኖችን ማዕድ በማጋራት ለራሱም ለወገኑም ያለዉን ክብርና ፍቅር ማሳየት ይገባል ማለታቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

