አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ፍትህ፣ የጸጥታ እና የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የዞን ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የፍትህ እና የጸጥታ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዶክተር ይልቃል÷ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይል፣ ፖሊስ፣ ሚሊሻና ፋኖ የህይወት እና የአካል መስዋዕትነት ከፍለው ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን ከአሸባሪው የህወሃት ቡድን ነጻ በማውጣት እና ቡድኑ በወረራቸው አካባቢዎች ላይ እዲቀበር ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡
እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ የሚከፍሉ የፀጥታ ሃይል፣ የፍትህና የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ሰራተኞች እንዳሉ ሁሉ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የፍትህ ተቋማት የፍትህ ስርዓቱን በማሻሻል እና ስርዓትን በማስፈን ህዝብ ፍትህ የሚያረጋግጥልኝ ተቋም ስለሆነ የኔ ተቋም ነው እንዲለው ለማድረግ ሃላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት ይገባል፤ ለዚህም ቁርጠኛ የሆነ ዳኛና አቃቤ ህግ መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ህግን ለማስከበር ቀን ከሌት የሚሰራና ቁርጠኛ የሆነ የፖሊስ ሰራዊት መገንባት እንደሚገባም ማስረዳታቸውን መገኘታቸውን ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሚሊሻ ሲቋቋም የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ቢሆንም በተለያዩ ግንባሮች በከፈለው መስዋዕትነት ታሪክ ሰርቷል ያሉት ዶክተር ይልቃል÷ ቀጣይም ለህዝብ እና ለሀገር የሚጠቅም አካባቢውን የሚጠብቅ ሚሊሻ መገንባት አለብን ብለዋል።
የአማራ ልዩ ሃይል ወደር የማይገኝለት፣ ቆራጥ፣ ጽኑ፣ ጀግናና የማይበገር ሰራዊት መሆኑን በማውሳት÷ ልዩ ሃይሉ የአማራ ህዝብ የጀግንነት መገለጫ ሆኖ እንዲቀጥል መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ፋኖ ሀገር ተወረረች ሲባል በከፍተኛ ንቅናቄ ተነስቶ ለአማራ ብሎም ለኢትዮጵያ መስዋዕትነት የከፈለ ሃይል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በቁርጠኛነትና መስዋዕትነት የሚጠይቅ ስራ በመስራት የህዝብን የፀጥታ፣ የፍትህና የደህንነት ጥያቄዎች መመለስ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

