አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በአንድ ዓመት ተገንብተው የሚጠናቀቁ 5 ሺህ ተገጣጣሚ ቤቶችን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጠ።
በግንባታ የማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአስተዳደሩ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ የሰሚን ወሃቢራቢ ፣ የኢትዮጵያ ኮንስታራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በአጠቃላይ በመዲናዋ 10 ሺህ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ይገነባሉ። በመጀመሪያው ምዕራፍ 5 ሺህ ተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ የሚካሄድ ሲሆን፥ ባለ አራት እና ዘጠኝ 9 ፎቆች የመኖሪያና የንግድ ቤቶች የሚያካትቱ ይሆናልም ነው የተባለው፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ አዲስ 5 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ በስምንት ቢሊየን ብር በጀት ያስጀመሩ ሲሆን፥ በዚሁ ወቅት በከተማዋ የነዋሪዎች መሠረታዊ የቤት ጥይቄ ለመፍታት ብዙ ጥረቶችና ዝግጅቶችን አድርገናል ብለዋል።
ተገጣጣሚ ቤቶቹን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን እንደሚገነባው ተገልጿል ።
የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ሃላፊ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ተገጣጣሚ ቤቶቹ በአንድ ዓመት ገንብቶ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ለግንባታው የሚውል ግብዓት ኮርፖሬሽኑ ባሉት ፋብሪካዎች አምርቶ ማጠናቀቁንም አንስተዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የቤቶች አስተዳደር ሃላፊ የሰሚን ወሃቢራቢ ፥ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን አቀናጅቶ በመምራት ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ዛሬ መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበት መሬት በህገወጥ መንገድ ተይዞ የነበረና ወደ መሬት ባንክ የተመለሰ መሆኑ ተነስቷል፡፡
ቤቶቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁ በከተማ ደረጃ የተያዘውን ቤቶችን ለዜጎች ተደራሽ የማድረግ ዕቅድ ለማሳካት እንደሚያግዝ
ይጠበቃል፡፡
በዘቢብ ተክላይ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

