አዲስ አበባ፣ጥር 16፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሳያውቁ አሸባሪውን የሸኔ ቡድን ለተቀላቀሉ የኦሮሞ ወጣቶች እጅ እንዲሰጡ ጥሪ አቀረበ፡፡
የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ፥ አሸባሪ ቡድኑ ሊያሳካ የሚፈልገው የፖለቲካ ዓላማ ኖሮት የማያውቅ እና ህዝባዊ መሠረት የሌለውም መሆኑን አስታውቋል።
የሽብር ቡድኑ የኦሮሞ ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዘርፍ ላይ ይህ ነው የሚባል አስተዋጽዖ ያላበረከተ ድርጅት መሆኑንም ነው ያመለከተው።
መግለጫው፥ ቡድኑ የኦሮሞን ህዝብ ማንነትና ክብር አዋርዷልም ነው ያለው።
ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ በፀረ ጭቆና ትግሉ ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሎ ወደ ሚገባው ክብር ሲወጣ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ግን ተቃውሟል ያለው መግለጫው፥ ይባስ ብሎም ይህ አሸባሪ ቡድን የኦሮሞን ህዝብ እየገደለና እያዋረደ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የክልሉ መንግስት ዘመኑን የሚዋጅ፣ በእውቀት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ባሕል እውን በማድረግ ሠላም የመረጡትን አሸባሪ ኃይሎች ለመመለስ ጥረት አድርጓል ብሏል።
አሸባሪ ቡድኑ ለሀገር ሲባል የተደረገውን ልመና እና ተማጽኖ ከመቀበል ይልቅ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ክህደትና ውርደት መፈፀሙን ነው ያነሳው፡፡
የሸኔ ዓላማ ኦሮሞን ማዋረድ እንደሆነ በርካታ ወጣቶች ተረድተው በተለያየ መንገድ እጃቸውን ለመንግስት እየሰጡ ከጥፋት ተመልሰዋል ብሏል መግለጫው፡፡
የተቀሩትም የሸኔ አመራሮች ከአሸባሪው የህውሓት ቡድን ጋር መሰለፋቸውን ሲያዩ እና አባ ገዳዎች የሠላም ጥሪ ሲያቀርቡ በሥራቸው በመፀፀት እጃቸውን ለመንግስት እየሰጡ መሆኑም ተመልክቷል።
ቢሆንም ግን አሁንም ቁጥራቸው በርካታ የሆነ ቡድኑን የተቀላቀሉ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች አላስፈላጊ መስዋትነት እየከፈሉ ነውም ብሏል መግለጫው፡፡
በስህተት ወደ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ለተቀላቀሉ የኦሮሞ ወጣቶች ተግባራቸው የተሳሳተ እና የኦሮሞን ህዝብ የሚያዋርድ እንደሆነ በመረዳት በወጣትነት እድሜያቸው እንዳይቀልዱ ጠይቋል።
የነገን ጠንካራ መሠረት መገንባት የምንችለው በወጣትነት ዘመናችን ትክክለኛውን አስተሳሰብ ስንከተልም ነው ብሏል መግለጫው ።
ወጣቶች የሚገባቸው፥ ትርጉም የለሽ መስዋዕትነት መክፈል ሳይሆን የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት አካል በመሆን ከክልሉ ጋር መበልፀግ ነው ያለው መግለጫው፥ ወጣቶች ባለን አቅምና እውቀት ከተጠቀምን የኦሮሞን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን መቀየር እንችላለን ነው ያለው።
የህዝቡ ሰላምና ብልፅግና እውን እንዲሆን ሰላማዊ ጥሪውን እንዲቀበሉና ወደ ልማት እንዲገቡ የክልሉ መንግስት ጥሪውን አቅርቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

