Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ውሎ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ ነው።
 
የኅብረቱ መሪዎች በትናንት ውሏቸው የአፍሪካን አንድነት የሚያጠናክሩና በአህጉሪቱ ላይ የሚታዩ የተዛቡ ትርክቶችን ለመቀየር የሚያስችሉ ሀሳቦችን አንስተው መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል።
 
በጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፥ የአፍሪካ ድምጽ በመላ ዓለም በአግባቡ መደመጥ እንዳለበትና አፍሪካ በጸጥታው ምከር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት።
 
ሌሎች ንግግር ያደረጉ የኅብረቱ መሪዎችም የአፍሪካን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እውን ለማድርግ የአፍሪካውያን ትብብርና አብሮነት በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ መናገራቸው ተገልጿል።
 
በሀገራት መካከል ትብብርን ማጠናከር፣ ግጭቶችን ማስቆም እንዲሁም የምግብ ዋስተናን ማጠናከር ከመሪዎቹ የትኩረት ነጥቦች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
 
በፓን አፍሪካኒዝም የትብብር መንፈስ ለአፍሪካ ልማት መትጋት፣ አንድነትን ማጠናከርና ዕድገትን ማፋጠን እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
 
የአፍሪካን ብልጽግና እውን ለማድርግ ከምንም አስቀድሞ አስተማማኝ ሰላምና የተረጋጋ የፖለቲካ አካሄድ እንደሚያስፈልግ እና በአፍሪካ ጎልቶ እየታየ ያለውን ኢ-ሕገ መንግስታዊ የመንግስት ለውጥ በጋራ ማውገዝና መታገል እንደሚገባም ተነስቷል።
 
የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔን ምክንያት በማድረግ ለመሪዎች የተዘጋጀ የእራት ግብዣ መርሀ ግብር ትናንት ምሽት በወዳጅነት ፓርክ የተካሄደ ሲሆን፥ ባህላዊ ሙዚቃና ሙዚቃዊ የውሃ ትርዒትም ቀርቧል።
 
35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ መወሰኑና ለመካሄድ መብቃቱ የኢትዮጵያን ገጽታ ሲያጠለሹ የነበሩ ኃይሎችን ያሳፈረ መሆኑም መገለጹ ይታወሳል።
 
ከትናንት ረፋድ ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው 35ኛው አፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ፥ ከሰዓት በኋላ መርሀ ግብሩም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በዝግ መክሯል፡፡ ዛሬም ውይይቱን በዝግ መቀጠሉ ታውቋል።
 
የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ለኀብረቱ መሪዎች 35ኛ ጉባኤ ያቀረቡትንና በአህጉሪቱ የወና በሽታን በመከላከል ረገድ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ጥረትና የተገኘውን ውጤት አስመልክተው ዛሬ መግለጫ እንደሚሰጡ ከኀብረቱ ደረገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በወባ በሽታ መከላከል ዙሪያ ለጉባኤው ፖርት ያቀረቡትና ለጋዜጠኞች መግለጫ የሚሰጡት የአፍሪካ መሪዎች የፀረ ወባ ኅብረት ሊቀመንበር በመሆናቸው ነው።
Exit mobile version