Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ማኪ ሳል ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምስጋና አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር እና የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን ላደረጉት ጥረት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምስጋና አቅርበዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል በኅብረቱ 35ኛ የመሪዎች ጉባኤ የመዝጊያ ስነ ስርአት ላይ ንግግር አድርገዋል።

ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል በዚሁ ንግግራቸው፥ ለ35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊ ለሆኑ መሪዎች ላደረጉት የሞቀ አቀባበል እና የኅብረቱ ጉባኤ የተሳካ አንዲሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምስጋና አቅርበዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኮቪድ ወረርሸኝ ፈተና በሆነበት ወቅት የኀብረቱ ስብሰባ የመከላከያ ዘዴዎችን በጠበቀ መልኩ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ሊቀመንበሩ አመስግነዋል።

የአፍሪካ ሀገራት አሸባሪነትን፣ መፈንቅለ መንግስት እና የመሳሰሉ ችግሮችን ማስወገድ እንዳለባቸው የገለጹት የኅብረቱ ሊቀመንበር፥ የአፍሪካን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በጋራ ልንሰራ ይገባል ነው ያሉት።

ከ600 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ ሃይል ሳያገኙ በጨለማ ውስጥ ይኖራሉ ያሉት የኅብረቱ ሊቀመንበር፥ አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን ለማስወገድ እና የተሻለ አህጉር እውን ለማድረግ ተባብረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኢኮኖሚ ትስስር፣ ጤና፣ ሰላምና ጸጥታ የአፍሪካውያን ቀጣይ የርብርብ አጀንዳዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አክለውም፥ ኅብረቱ የላቀ የአመራር ጥበብ ተጠቅሞ አፍሪካን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰራ ጽኑ እምነት አለኝ ያሉት የኅብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር፥ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽኑን ለሚያደርገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

ህብረቱ በሥሩ ያሉ የአደረጃጀት ችግሮችን ተቋቁመው እየሰራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማሃመት በበኩላቸው 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ ስኬታማ ነበር ብለዋል።

ምንም እንኳን አህጉሪቱ በተለያዩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች ውስጥ ብትሆንም ህብረቱ የአፍሪካን ችግሮች ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ሙሳ ፋኪ ማኸመት በመዝጊያቸው እንደ ኢ ህገመንግስታዊ የመንግስት ለውጥን የመሳሰሉ የፖለቲካ አለመረጋጋት ችግሮችን ከምንጫቸው ለመቅረፍ ጥረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

መፈንቅለ መንግስት አሸባሪነትን ለማስወገድም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት መፍትሄ አይሆንም ነው ያሉት።

መፈንቅለ መንግስትም ሆኑ ሌሎች ህገወጥ ወታደራዊ እርምጃዎች የአህጉሪቱን ገጽታ ከማጠልሸት ባለፈ ችግሮችን የሚያባብሱ በመሆናቸው ሊወገዙ ይገባል፤ ፈጽሞ ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል።

በወንደሰን አረጋኸኝ

 

Exit mobile version