Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን ባካሄደው ወረራ ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን ባደረሰው ወረራና ጥቃት ከ300 ሺህ በላይ ዜጎችን ማፈናቀሉን የአፋር ብሄራዊ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባብሪያ ጽ/ቤት ገለጸ።

የጽ/ቤቱ ሃላፊ አቶ መሓመድ ሁሴን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ፥ አሸባሪው ህወሓት በመጀመሪያው ዙር ወረራው በአፋር እና በአማራ ክልሎች የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል፥ የትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆነው ኪልበቲ ረሱ ዞን እየፈጸመ ባለው የበቀል ጥቃት የአበአላ፣ ኮናባ፣ እሪፕቲ፣ መጋሌ፣ ከፊል ዳሎ እና በረሃሌ ወረዳ ነዋሪዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል ብለዋል።

ይህንን ተከትሎ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በ14 የመጠለያ ጣቢያ የተጠለሉትን ክልሉ በሚችለው አቅም የሰብዓዊ ድጋፍ የማድረስ ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ፥ ከዚህ ባለፈ ግን የሽብር ቡድኑ የሚያደርስብንን በደል አንሸከምም ብለው በዱር በገደሉ ተበትነው የቀሩ ዜጎች መኖራቸውንም ሃላፊው ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድን ወርሮ በያዛቸው አካባቢዎች ላይ የቀሩ ዜጎች ላይ የከፋ የሰብዓዊ ችግር እያደረሰባቸው መሆኑንም የአፋር የመረጃ መንገድ በሆነው የዳጉ ስርዓት መገንዘብ ችለናል ብለዋል።

ሆኖም የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ የማይቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች መድረስ አልተቻለም ነው ያሉት።

በአፋር ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር የመጨረሻ መፍትሄ እንዲያገኝ ለማድረግ እና የአኘባሪና ወራሪውን ቡድን ቀንበር ከጫንቃው ለማውረድ መንግስት እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም ነው አቶ መሃመድ የጠቆሙት።

እነዚህ በትግራይ ክልል አጎራባች አካባቢ የሚገኙ ወረዳዎች ያሉበት መልክዓ ምድር ዝቅተኛ መሆኑ እና የወራሪው ቡድን ከፍ ባለ ቦታ ላይ ሆኖ ዜጎችን በከባድ መሳሪያ ለማጥቃት ምቹ ሁኔታን ስለፈጠረለት ብዙ ነዋሪዎችን ለከፋ ሲቃይ ዳርጓል ብለዋል።

ይሄንን ችግር የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ እና የአፋር ህዝብም ከአሸባሪው ህውሓት ነፃ እንዲሆን የፌደራሉ መንግስት ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ያሉት አቶ መሃመድ ፥ ላለፈው አንድ ዓመት የአፋርና አማራ ህዝብ ላይ ወራሪው ቡድን ሲያደርስ በቆየው ውድመት ከአፋር ህዝብ ጎን የነበራችሁ ኢትዮጵያውያን አሁንም የአፋር ህዝብ የከፋ ችግር ውስጥ ስለሆነ ልትደርሱለት ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

ከዚህ ባለፈም ዓለማቀፍ የረድኤት ተቋማትም በከፋ ችግር ውስጥ ላለው የአፋር ህዝብ ሊደርሱለት እንደሚገባ ሃላፊው ጥሪ አስተላልፈዋል።

በይስማው አደራው ፣ ሰዓዳ ጌታቸውና ኢብራሂም ሙሳ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version