ልማትን በመዋዕለ-ንዋይ መደገፍ፣ የጤና ሥርዓት እና ክትባት ማምረት፣ ግብርና እና ዘላቂ ልማት፣ ትምህርት፣ ባሕል እና የሙያ ሥልጠና፣ ስደት እና መፈናቀል፣ የግሉን ዘርፍ መደገፍ እና የኢኮኖሚ ትሥሥር መፍጠር፣ ሠላም፣ ደኅንነት እና አሥተዳደር እንዲሁም የዓየር ንብረት ለውጥ፣ የኃይል አማራጭ፣ ዲጂታል ግንኙነት እና የትራንስፖርት አገልግሎት ግንባታ በክብ ጠረጴዛ ውይይት እና ክርክር እንዲደረግባቸው የተለዩ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተለያዩ የአውሮፓ እና የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች እና በሚነሱት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እውቀቱ ያላቸው ተጋባዥ ምሁራን እንደሚሳተፉ እና ሙያዊ ምልከታቸውንና የመፍትሄ ሃሳቦቻቸውን እንደሚያቀርቡ የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት በመረጃው ይፋ አድርጓል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት- አፍሪካ ኅብረት የ2030 የጋራ ራዕይ መግለጫ በተሳታፊዎች ይፀድቃል ተብሎም ይጠበቃል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ዴር ሌየን በአውሮፓ ኅብረት – አፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር “ሥራ ስንጀምር አፍሪካ ቁልፍ የአውሮፓ አጋር እንደምትሆን አውቅ ነበር” ብለዋል።
አፍሪካ እና አውሮፓ ሠላም እና ደኅንነትን ለማረጋገጥና ለመበልጸግ ተመሣሣይ ራዕይ ያላቸው አህጉራት መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡
አህጉራቱ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በተለይ በሰው ኃይላቸው ላይ መሥራት እንደሚገባቸው እና በግልጽነት ላይ የተመሰረተ መልካም አስተዳደር እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ በተለይ ከጸሃይ እና ከንፋስ በሚገኝ ታዳሽ ኃይል የታደለች አህጉር እንደሆነችና አውሮፓም ይህን ኃይል አፍሪካ ለመጠቀም የምታደርገው ጥረት መደገፍ እንደሚገባት ነው የጠቆሙት፡፡
የትራንስፖርት መሠረተ – ልማትን በተመለከተም የባቡር መንገድና የአስፋልት መንገድ ግንባታዎች አፍሪካ በሚኖራት የተሳሰረ ነጻ የንግድ ግንኙነት የላቀ ሚና እንደሚኖራቸውም ነው የተናገሩት፡፡
የኢንተርኔት ተደራሽነት እና የሳተላይት ግንኙነት ላይ አህጉራቱ በጥምረት በመስራት የበለጠ መተሳሰር እንዳለባቸው ኡርሱላ ዴር ሌየን አሳስበዋል፡፡

