አዲስ አበባ ፣ የካቲት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ነጻ በሆነች ሀገር ዐድዋን ማክበር የቻልነው አባቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ አያቶቻችን እና ቅድመ አያቶቻችን ባፈሰሱት ደምና በከፈሉት ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ በ126ኛው የዐድዋ ድል በአል ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ዐድዋ አባቶቻችን፣ አያቶቻችን እና ቅድመ አያቶቻችን ከፍተኛ መሥዋዕትነትን የከፈሉበትና በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ቦታ የያዘ የድል በዓል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
አያይዘውም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች “ከቅኝ ግዛት ሞት ይሻላል ብለው በከፈሉት መስዋዕትነት ላይ ቆመን በዓሉን እያከበርን መሆኑ ለአፍታም መዘንጋት የለበትም” ነው ያሉት።
“የነጻነት ዋጋ የሚለካው ነጻነት የተነፈጋቸውን ሀገራት ታሪክ ስንመረምር ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ ቀና ብለን የቆምነው ወራሪን ማሸነፍ እንደሚቻል በማሳየታችን ነው ብለዋል።
በዐድዋ ድል ለተጨቆኑ ህዝቦች ሁሉ ወራሪን እና ቅኝ ገዢነትን ማሸነፍ ይቻላል የሚለውን መልዕክት ማስተላለፍ መቻሉንም አስታውሰዋል።
“ወደድንም ጠላንም የአድዋ ድል በዓል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ቀዳሚ ቦታ የሚይዝ ቢሆንም ለሌሎች ህዝቦችም አኩሪ ታሪካዊ የድል በዓል ነው” ብለዋል ባስተላለፉት መልዕክት፡፡
ፕሬዚዳንቷ በመልዕክታቸው እንደሀገር ለማደግ መሠረትን ማጠናከር እና ታሪክ ላይ የጋራ መግባባት መያዝ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
ታሪክን ለታሪክ ጸሃፊዎችና ተመራማሪዎች በመተው ከጊዜያዊ ጉዳይ ባለፈ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ታሪክን ያልተጋፈጠ ህዝብ የወደፊቷን ኢትዮጵያ በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት እንደሚቸገርም አውስተዋል።
ኢትዮጵያን ለዓለም ማሳየት ያለብን ከዐድዋ እሴት ጋር አያይዘን እንጂ በመከፋፈል እና እርስ በእርስ በመዋጋት ሊሆን እንደማይገባም አንስተዋል።
ኢትዮጵያን መገንባት የሚቻለውም የዐድዋን መንፈስና ቅርስ በመያዝ የሚከፋፍለንን ትተን ለአንድ ዓላማ ስንቆም ብቻ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ።
ከመፈክር በላይ በተግባር አንድነትን እና ዐድዋን ማሳየት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ከእርስ በእርስ ጦርነት በመውጣትም በዐድዋ ላይ የታየውን ገድል ኢትዮጵያን ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት በማውጣት መድገም እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በዓለማየሁ ገረመው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

