አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክ/ከተሞች በመዘዋወር የከተማ ግብርና ስራዎች ያለበትን ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የከተማ ግብርና እንቅስቃሴዎች ለሀገር አቀፍ የምግብ ዋስትና እንቅስቃሴዎች ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው በተደጋጋሚ መግለፃቸው የሚታወቅ ሲሆን ÷ዛሬም በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የቤተሰብና የአካባቢ የከተማ ግብርና እንቅስቃሴዎች ያሉበትን ደረጃ ተዘዋውረው መመልከታቸውን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ጉብኝቱን በተመለከተ ከንቲባ አዳነች አበቤ እንደገለጹት፥ በመዲናችን በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተካሄዱ ያሉት የከተማ ግብርና ስራዎች ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ አላቸው ።
ከንቲባዋ አክለውም፥ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችንም የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መድበን ብዙ ምርቶች ወደ ገበያ ከማስገባት በተጨማሪ በየግቢያችን በማምረት ጫናውን ማቅለል እንደሚቻል ማሳያ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል ።
ከዚህ በፊት ከቆሻሻ መጣያነት ያለፈ ጥቅም የማይሰጡ የከተማዋ ክፍት ቦታዎች ለከተማ ግብርና ማሳዎች እንዲውሉ አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት ።
“እነሆ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ጓሮ ያመረተውን አትክልት የምንመገብበት ጊዜው እሩቅ አይሆንም” ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው መልዕክታቸውን አስፍረዋል።

