አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
ትናንትና ምሽት ላይ የከተማ አስተዳደሩ ግብረ ሀይል ባደረገው አሰሳ ዘይት ከከተማዋ ተጭኖ ሲወጣ መያዙንም ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሰዓት በተለየ ሁኔታ ዘይትም ሆነ ሌሎች ሸቀጦች ላይ ዋጋ ለመጨመር የሚያስገድድ ምንም አይነት ሁኔታ እንደሌለ የገለጹት ከንቲባዋ የምርት እጥረት ቢኖርም ያለውን ምርት ደግሞ ለህብረተሰቡ ማቅረብ ተገቢ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩም የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የእሁድ ገበያን የማስፋፋት ስራ እየሰራ መሆኑንና አስፈላጊ የሚባሉ ምርቶች መቅረባቸውን ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ከዚህ ባለፈም ከተማ አስተዳደሩ 1 ቢሊየን ብር በጅቶ ለሸማች ማህበራት በማሰራጨት ገበያውን ለማረጋጋት እንዲጠቀሙበት እያረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በትክክል ለህዝቡ ስለመድረሱ ክትትል እንደሚደረግና በጀቱ የተመደበው ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ስለሆነ ለግል ጥቅም የሚያውሉ ሸማቾች ላይ ከተማ አስተዳደሩ ምህረት የለሽ እርምጃ እንደሚወሰድም ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
ከፍተኛ በጀት ከሌሎች ፕሮጀክቶች ቀንሰን የመደብነው ህዝባችን ጋር እንዲደርስ ነው፤ ማንም ባቋራጭ መንገድ እንዲከብርበት አይደለም ያሉት ከንቲባዋ÷በዚህ መንገድ የሚመጣ ማንኛውም እጥረት ምህረት የለሽ እርምጃ እንወስድበታለን ብለዋል፡፡
በዘቢብ ተክላይ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

