አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በፀጥታ ሃይሉ በተወሰዱ እርምጃዎች አንጻራዊ ሰላም እየታየበት መምጣቱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በደቡብና በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና የጸጥታ ችግሮች መታየት ከጀመሩ ሰነባብቷል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ መርዳሳ እንዳሉት፥ በአካባቢው የለውጥ እንቅስቃሴውን ለማደናቀፍ ላለፈው አንድ ዓመት የታጠቁ ሃይሎች ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል።
እነዚህ ሀይሎች በአካባቢው የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የጸጥታ አካላት ላይ ግድያን ጨምሮ ጥቃቶችን ሲፈፅሙ መቆየታቸው በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል ነው የተባለው።
ታጣቂ ኃይሉ ባለሀብቶችን፣ ግለሰቦችን፣ የመንግስት አመራሮችና የጸጥታ ኃይል አባላትን ሳይቀር በመግደል በከተሞችና ገጠር አካባቢዎች በርካታ ጥፋቶችን አድርሷል።
ሆኖም መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም ሊሳካ ሳይችል መቅረቱን ያነሱ ሲሆን፥ መንግስትም የህግ የበላይነትን ለማስከበር ወደ እርምጃ መግባቱን ኮሚሽሩ ገልጸዋል።
ምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች፣ ደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ታጣቂ ኃይሉ የሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች መሆናቸውንም ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።
በመሆኑም የመንግስት የጸጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በመተባበር በታጣቂ ቡድኑ ላይ በተወሰደው እርምጃ አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ትብብርም አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ