አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው ለቀቁ።
ዓየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ አቶ ተወልደ በፈቃዳቸው ከሀላፊነት መልቀቃቸውን አስታውቋል።
አየር መንገዱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፥ አቶ ተወልደ ላለፉት ስድስት ወራት ህክምናቸውን በአሜሪካ ሲከታተሉ መቆየታቸውን አስታውሷል፡፡
አቶ ተወልደ ገብረማርያም በግል የጤና እክል ምክንያት የአየር መንገዱ ዋና አስፈጻሚ ሆነው መቀጠል እንደማይችሉ በመግለጽ የስራ አመራር ቦርዱ የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡
በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስራ አመራር ቦርድ በዛሬው ዕለት ባካሄደው ስብሰባው አቶ ተወልደ ያቀረቡትን የስራ መልቀቂያ ጥያቄን መቀበሉን አስታውቋል፡፡
የስራ አመራር ቦርዱ በአቶ ተወልደ ገብረማርያም ምትክ ለአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጸሚ በቅርቡ እንደሚመድብም ነው የገለፀው።
አየር መንገዱ በመግለጫው አቶ ተወልደ ከአንድ አስርት ዓመታት በላይ ተቋሙን በመሩበት ወቅት ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ መሆናቸውን አመልክቷል።
በእርሳቸው አመራር አየር መንገዱ በሁሉም መለከያ የተለየ ስኬት ማስመዝገቡን በመጠቆምም ዓመታዊ ገቢው ከ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ተነስቶ አሁን ላይ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መብለጡን ጠቁሟል።
33 የነበሩት የአውሮፕላን ቁጥሮችም ወደ 130 ማደጋቸውን እና በዓመት የሚያስተናግደው የመንገደኞች ቁጥር ከ3 ሚሊየን ወደ 12 ሚሊየን ከፍ ማለቱን አስታውቋል።
በአጠቃላይ በእርሳቸው አመራር አየር መንገዱ በአራት እጥፍ አድጓል ያለው መግለጫው፥ 700 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያወጡ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን አየር መንገዱ የገነባው በእርሳቸው አመራር መሆኑን በመግለፅም፥ በአፍሪካ ትልቅ የሚባለን ሆቴል፣ የካርጎ ተርሚናል፣ የአቭዬሽን አካዳሚ እና የበረራ ሲሙሌተሮች መገንባታቸውን ለአብነት ጠቅሷል።
የስራ አመራር ቦርዱ፣ ከፍተኛ አመራሮች እና ሰራተኞች በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቤተሰብ ለዚህ አስተዋፅኦዋቸው ከፍ ያለ ምስጋና እንዳላቸው በመግለፅ መልካም ጤናን ተመኝቷል።