Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የብሔረሰብ ስያሜው “ቤኒሻንጉል” እንዲሆን ወሰነ

 

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በርታ ተብሎ ሲጠራ የነበረውን የብሔረሰብ መጠሪያ “ቤኒሻንጉል” ተብሎ እንዲሰየም የቀረበለትን የብሔረሰብ መጠሪያ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ፡፡

የብሔረሰቡን ስያሜ በተመለከተ የብሔረሰብ ምክር ቤቱ ቀደም ሲል በኩርሙክ ወረዳ ባካሄደው ጉባዔ የብሔረሰቡን ታሪክ መሠረት ባደረገ መልኩ “ቤኒሻንጉል” ተብሎ እንዲጠራ የቀረበውን መጠሪያ ማጽደቁ የሚታወስ ነው፡፡

በዛሬው ዕለት የብሔረሰብ መጠሪያው “ቤኒሻንጉል ብሔረሰብ” ተብሎ እንዲጸድቅ ለክልሉ ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን፥ ምክር ቤቱ ውይይት ካደረገ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የክልሉን ያልተማከለ የወረዳ አካባቢ አስተዳደርን ለማጠናከር የቀረበውን የማሻሻያ አዋጅ በመመርመር የአሶሳ ወረዳ በሁለት ወረዳዎች እንዲዋቀር አጽድቋል፡፡

ወረዳው ካለው የቆዳ፣ የቀበሌ እና የሕዝብ ብዛት፣ የአስተዳደር ምቹነት፣ ለህዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በወቅቱ ምላሽ ለመስጠት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ምቹነት አኳያ በመወያየት ወረዳው በሁለት ወረዳዎች እንዲዋቀር የቀረበው የማሻሻያ አዋጅ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡

በማሻሻያ አዋጁም አሶሳ ወረዳ የሚለው ቀርቶ “ኡራ ወረዳ” እና “አብርሃሞ ወረዳ” ተብሎ በሁለት ወረዳዎች የተዋቀረ ሲሆን÷ በዚህም ለህዝብ አስተዳደር በሚመች መልኩ ኡራ ወረዳ 41 እንዲሁም አብርሃሞ ወረዳ ደግሞ 41 ቀበሌዎችን እንዲኖሯቸው በማድረግ መደራጀታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ምክር ቤቱ የ2014 ዓ.ም የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትን እና የቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ሚሊሻ ጽ/ቤትን እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ላይ ተወያይቶ በማጽደቅ 13ኛ መደበኛ ጉባዔውን አጠናቋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version