አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ ሰላምና የህዝቦችን ደህንነት በማረጋገጥ ልማትና ዕድገትን ማስቀጠል እንዲቻል ወጥነት ባለው አሰራርና በተደራጀ ዕቅድ መመራት አለብን ሲሉ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕስ መስተዳድር ሽመለስ አብዲሳ ተናገሩ።
የግምገማው መድረክ ሲጀመር ርዕስ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባደረጉት ንግግር፥ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ፣ የህዝቦችን ደህንነት በማረጋገጥ ልማትና ዕድገትን ለማስቀጠል ወጥነት ባለው አሰራርና በተናበበ ዕቅድ መመራት አለብን ብለዋል።
አቶ ሽመልስ በክልሉ የሚስተዋሉትን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር እጦት አንስተዋል።
የ2015 በጀት ዓመት የክልሉ የልማት ዕቅድ፣ የኑሮውድነት፣ የወጣቶች የስራ አጥነት ችግሮች እንዲሁ በመድረኩ ትኩረት የሚደረግባቸውና ቀጣይ በአፈፃፀም ተለይተው አቅጣጫ እንደሚሰጥባቸው ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት የአፈፃፀም ክንውኑ በተቀመጠው እቅድ ልክ ስለመሆኑ፣ አቅጣጫና አሰራሩ ተጠብቆ ስለመካሄዱ፤ በአፈጻጸም ሂደቱ የነበረው ቁርጠኝነት፣ የታዩ ክፍተቶችና ችግሮችን ለመፍታት በተለይም ህዝቡን ከማሳተፍና የሀብት ብክነትን ከመቀነስ አንጻር ያለው ሁኔታ በመድረኩ እንደሚገመገም አስታውቀዋል።
ሌብነትን ከመከላከልና በህዝባዊ መድረኮች የተነሱ ጉዳዮችን በባለቤትነት ከመፈፀምና ከማስፈፀም አንፃር በትክክል ፈትሸን ቀጣይ አቅጣጫ እናስቀምጣለን ሲሉ ርዕስ መስተዳድሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

