Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመጀመሪያው የወጣቶች ሃገር አቀፍ ኦሊምፒክ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 21 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው የወጣቶች ሃገር አቀፍ የኦሊምፒክ ጨዋታ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ተጀምሯል።
 
በጨዋታው ከአማራ ክልል ውጭ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ስፖርተኞች ተሳታፊዎች መሆናቸው ተገልጿል።
 
በመክፈቻ ስነ ስርአቱ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተወካዮች እና እውቁ ኬኒያዊ አትሌት ፖል ቴርጋት ተገኝተዋል።
 
ጨዋታው ከዛሬ ግንቦት 21 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ ይሆናል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ÷ ኦሊምፒክ – በስፖርት ልምምድ ፣ በማስተማር ፣ በጓደኝነት ፣ በመተሳሰር እና በፍትሃዊ ጨዋታ አሸናፊነትን ማግኘት መሆኑ የአንድነትና የሠላም ተምሳሌት ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ በመሳተፍ የአሸናፊነትና የጽናት ተምሳሌት እንደሆነች እንዲሁም ኦሊምፒክ ትልቅ ሀገራዊ ኩራቷ ሆኖ እንደቀጠለ ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ÷ የኦሊምፒክ ጫወታ መከፋፈልን የማይፈቅድ እና የወንድማማችነትን እሴት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ÷ የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ውድድር መደረጉ በመሰል ጨዋታዎች አሳሳቢ የሆነውን የዕድሜ ማጭበርበር ለማስቀረት መሠረት እንደሚሆን ጠቅሰው በቀጣይም ውድድሩ በትምህርት ቤቶች ደረጃ እንዲወርድ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ማኅበር ዋና ጸሐፊ ኢንጂነር አሕመድ አብዶ ሀሺም ÷ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኩራት የወንድማማችነታችንና የአንድነት መሠረት ነው ብለዋል።

 
በጌታቸው ሙለታ
Exit mobile version