የመጀመሪያው የወጣቶች ሃገር አቀፍ ኦሊምፒክ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ተጀመረ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ÷ ኦሊምፒክ – በስፖርት ልምምድ ፣ በማስተማር ፣ በጓደኝነት ፣ በመተሳሰር እና በፍትሃዊ ጨዋታ አሸናፊነትን ማግኘት መሆኑ የአንድነትና የሠላም ተምሳሌት ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ በመሳተፍ የአሸናፊነትና የጽናት ተምሳሌት እንደሆነች እንዲሁም ኦሊምፒክ ትልቅ ሀገራዊ ኩራቷ ሆኖ እንደቀጠለ ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ÷ የኦሊምፒክ ጫወታ መከፋፈልን የማይፈቅድ እና የወንድማማችነትን እሴት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ÷ የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ውድድር መደረጉ በመሰል ጨዋታዎች አሳሳቢ የሆነውን የዕድሜ ማጭበርበር ለማስቀረት መሠረት እንደሚሆን ጠቅሰው በቀጣይም ውድድሩ በትምህርት ቤቶች ደረጃ እንዲወርድ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ማኅበር ዋና ጸሐፊ ኢንጂነር አሕመድ አብዶ ሀሺም ÷ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኩራት የወንድማማችነታችንና የአንድነት መሠረት ነው ብለዋል።