Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሪፎርሙ በኋላ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሪፎርሙ በኋላ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከለውጡ በፊት 100 አውሮፕላን እንደነበሩት ጠቁመው፥ አሁን ላይ 135 መድረሱን ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ ከለውጡ ወዲህ 35 በመቶ የአውሮፕላን እድገት ማሳየቱንም አስታውቀዋል፡፡

ከለውጡ በፊት አየር መንገዱ 115 መዳረሻዎች እንደነበሩት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ 127 መዳረሻዎች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡

ከገቢ አንጻርም 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ የነበረው አየር መንገዱ ገቢውን ወደ 4 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ገቢ ላይ እንደደረሰ ነው የተናገሩት፡፡

ከመንገደኞች ቁጥር አንጻርም 6 ሚሊየን መንገደኞችን ያስተናግድ የነበረው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አሁን 22 ሚሊየን መንገደኞችን እያስተናገደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በተያያዘም 38 ሚሊየን ደንበኞች የነበሩት ኢትዮ ቴሌኮም 65 ሚሊየን ደንበኞች ላይ መድረሱን አንስተው፥ 33 ነጥብ 5 ቢሊየን የነበረው የተቋሙ ትርፍ 55 ቢሊየን ብር መድረሱን አስረድተዋል።

በኢትዮ ቴሌኮምና በኢትዮጵያ አየር መንገድ የታዩ ለውጦች መልካም ቢሁኑም አሁንም በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከመንገድ አውታር ጋር በተያያዘ በሰጡት ምላሽ ከለውጡ በፊት ሀገር አቀፍ ሽፋኑ 127 ሺህ ኪሎ ሜትር መሆኑን ገልጸው ከለውጡ በኋላ ግን 165 ሺህ ኪሎ ሜትር መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 60 ሜትር ስፋት ያለው 151 ኪሎ ሜት በአስፋልት ደረጃ መሰራቱን እና ከአስፋልት ውጭ ደግሞ 470 ኪሎ ሜትር መንገድ መሠራቱንም ነው የተናገሩት።

በአጠቃላይ ከለውጡ ወዲህ 22 ሺህ ኪሎ ሜትር በመገንባት ላይ መሆኑን ጠቁመው፥ በዘርፉ ያለው ስራ አመርቂ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ነው ያነሱት።

ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ ባለፉት ሶስት አመታት ከ2 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰው 15 ሺህ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብቷል ብለዋል፡፡

1 ነጥብ 7 ሚሊየን ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ በትምህርት ቤት ምገባ እንደሚያገኙ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ታምርት የተሰኘ ንቅናቄ በቅርቡ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

ከለውጡ በኋላ ሶስት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ እና 9 ኢንዱስትሪያል ፓርኮች በድምሩ 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋልም ብለዋል።

እንደ ሀገር የአፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌን (አጎዋ) ሳንጠቀም የውጪ ንግድ አድጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን የመተካት ሥራም ተሰርቷል ብለዋል።

ግብርናን የማዘመን ሥራ በስፋት እንደተሰራ እና የኩታ ገጠም ግብርና 45 በመቶ መድረሱን አስታውሰዋል።

ለግብርና የሚሰጠው የብድር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን በመጥቀስም፥ ዘንድሮ ብቻ መንግሥት ለማዳበሪያ 15 ቢሊየን ብር (በኩንታል ከ1 ሺህ ብር በላይ) መደጎሙን አመላክተዋል።

የዋጋ ግሽበትን በተመለከተም የብሩ ዋጋ ከመጠን በላይ ከመለጠጡ የተነሳ መስተካከል ነበረበት ያሉ ሲሆን ፥ የኢትዮጵያ ብር ዋጋ መቀነሱ ለዚህ ሁሉ ለውጥ መምጣት ምክንያት ሆኗልም ነው ያሉት።

የውጪ ምንዛሬ ለሰባት አመታት እየቀነሰ የነበረ ቢሆንም በዚህ የዋጋ ማስተካከያ እንዲጨምር ሆኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፥ 59 በመቶ ያህል ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት የኢትዮጵያ ሀብት ዕዳ ነበር ፤ ይህም ወደ 50 ነጥብ 5 መውረዱን አስረድተዋል።

የዋጋ ግሽበትን በተመለከተም በተለያዩ አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ምክንያቶች እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነትን ከሌሎች ዓለም አገራት ካለው የዋጋ ግሽበት ጋር በንፅፅር ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአገሪቱ በአሁኑ ሰአት ያለው የዋጋ ግሽበት 33 በመቶ መድረሱን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ያለው የኑሮ ውድነት ከፍተኛ እንደሆነ እና በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ ላለው ህብረተሰብ ጉዳቱ ከፍተኛ እንደሆነም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።

ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት መብራት፣ ውኃ፣ ማዳበሪያ እና ነዳጅን ጨምሮ በርካታ ነገሮች ላይ ድጎማ እንደሚያደርግ አስታውሰዋል።

የነዳጅ ድጎማን አስመልክቶ መንግስት ከሚቀጥለው ሐምሌ ወር ጀምሮ ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን ብቻ መደጎም እንደሚጀምርም አመላክተዋል።

በዚህም መንግስት በትራንስፖርት ለሚጠቀመው እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የድጎማው ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በዋጋ ግሽበቱ የሚጎዳው በዝቀተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምርት እጥረትና የፍላጎት ዕድገት፣ የገበያ ስርዓት፣ የአምራችነት መስተጓጎል፣ የፋይናንስ አጠቃቀም መንስኤዎች ናቸው ብለዋል።

ማዕድ ማጋራት በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ቤተሰቦች መጥቀሙን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአቅመ ደካሞች 8 ሺህ ቤቶች ታድሰዋል ተጨማሪም እየታደሰ መሆኑን አንስተዋል።

Exit mobile version