Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አለም አቀፍ የሴቶች ቀን እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ )የዘንድሮው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሴቶችን የእኩልትና የፍትሃዊነት ችግሮችን ለመፍታት እንቅስቃሴ የተጀመረበት ቀን መሆኑን ይገለጸል፡፡

ስለሆነም የዘንድሮው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ109ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ44ኛ ጊዜ በመከበር ላይ ነው፡፡

በሀገራችን የሚከበረው የሴቶች ቀን “የሴቶች ደህንነትና መብት መከበር ለሰላማችንና ለህልውናችን መሰረት ነው” በሚል መሪ ቃል ነው በተለያዩ ፕሮግራሞች እየተከበረ የሚገኘው፡፡

በዚህ መሪ ቃል መከበሩ የሴቶችን መብትና ደህነት ማስከበር እንዲሁም በሁሉም መስኮች ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግና ጥቅማቸውን ማስጠበቅ የስርዓተ – ጾታ እኩልነትን ከማስፈን ባሻገር ድህነትን በመዋጋት የዘላቂ ልማት ግቦችን እውን ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዚያም ባለፈ መሪ ቃሉ ሴቶች ለማህበረሰብ ለውጥ፣ ለአገር እድገትና ብልጽግና በአጠቃላይም ለሰላማችንና ለህልውናችን ወሳኝና ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ለማህበረሰቡ አጽዕኖት ሰጥቶ ለማስገንዘብና የሴቶችን መብትና ደህንነት በማስከበር ረገድም የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ የጋራ መግባባት ለመፍጠር መሆኑን ከሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም ዛሬ እየተከበረ ያለውን የሴቶች ቀን አስመልክትው በትናትናው እለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህ መልዕክታቸው የሴቶችን በዓል የምናከብረው የሁላችን በዓል ስለሆነ ነው፡፡በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን የቆምነው እናቶቻችን በከፈሉት ዋጋ በመሆኑ በዓሉ ልዩ ይሆንብናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የኖረች ሀገር ናት ስንል አሳፍረው የሚያስከብሯት እናቶችና እኅቶች ነበሯት፤ አሏት ማለታችን ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

አያይዘውም ኢትዮጵያ በነጻነት ጸንታ እንድትኖር እናቶቻችንና እኅቶቻችን በአራት ዐውደ ግንባር ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ጀግና ፈጥረዋል፤ ለጀግና የሚሆነውን ስንቅ አዘጋጅተዋል፡፡ ጀግኖችን ተንከባክበዋል፡፡ እነርሱ ራሳቸውም በጀግንነት ተዋግተው ድል አድርገዋልም ብለዋል፡፡

ማርች ስምንትን ስናከብር ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ ተከብሮ፣ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ፣ በክብርና በነጻነት እንድትኖር ለማድረግ እናቶቻችንና እኅቶቻችን እንደገና የሚነሡበት ቀን እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለንም ነው ያሉት፡፡

Exit mobile version