Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሐረሪ ክልል ካቢኔ የ2015 ረቂቅ በጀት ከ3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ እንዲጸድቅ ለክልሉ ምክር ቤት መራ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) በ2015 በጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት ረቂቅ በጀት ከ3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ እንዲጸድቅ ለክልሉ ምክር ቤት መርቷል፡፡

የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በ2015 የበጀት ዓመት በጀት እና በሐረር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ላይ ተወያይቷል።

በውይይቱም በ2015 ዓ.ም የክልሉ መንግሥት ረቂቅ በጀት ከ3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

ካቢኔው በክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የቀረበለትን የ2015 የበጀት ዓመት ረቂቅ በጀት መርምሮ ለክልሉ ምክር ቤት መርቷል።

በጀቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ14 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ተገልጿል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ÷ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ እና የሕዝቡን ችግር ሊቀርፉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በ2015 የበጀት ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና ወደ ሥራ እንዲገቡ ትኩረት ይሰጣልም ብለዋል።
በተለይም በገጠርና ከተማ የሕዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ሊመልሱ በሚችሉ ተግባራት ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ እንዲሁም የከተማውን የመጠጥ ውሃ ችግር እንዲቀረፍ ርብርብ እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ በበኩላቸው÷ ለውጥ ሊያመጡ እና አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎችን ሊመልሱ በሚያስችሉ ስራዎች ላይ በጀቱ ስራ ላይ መዋል አለበት ብለዋል፡፡
ድህነት ተኮር ዘርፎችን ቅድሚያ በመስጠት፣ ሃብትን በቁጠባና ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠቀም ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version