አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጃፓኑ ፊቸርበድ ኢንተርናሽናል ሊሚትድ ኩባንያ ጋር የ360 ሚሊየን ብር የመንገድ ጥገና ማሽነሪ ግዢ የውል ስምምነት ተፈራረመ።
በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የገንዘብ ድጋፍ በኩል የተመቻቸውን የመንገድ ጥገና ማሽነሪዎች ግዢ ስምምነት÷ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አንጂነር ሞገስ ጥበቡ እና የጃፓኑ ፊቸርበድ ዓለም አቀፍ ሊሚትድ ድርጅት ተወካይ አያሚ ናካዎ ጋር በበይነ መረብ ተፈራርመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትጵያና ጃፓን ግንኙነት ከ90 ዓመታት በላይ የቆየ መሆኑን ጠቁመው÷ ወሳኝ በሆኑ የትምህርት እና የቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አድንቀዋል።
ዛሬም ያልተቋረጠ ድጋፍቸው ለከተማችን በትራንስፖርቱ ዘርፍ ወሳኝ በሆነው መንገድ ጥገና በሚጠቅም መሳሪያ ግዥ ደግፈውናል ብለዋል።
ድጋፉ በኢዲስ አበባ የተሻለ የመንገድ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ የገለጹት ከንቲባ አዳነች÷ አቅራቢ ድርጅቱም በወቅቱ እንደሚያቀርብ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በበኩላቸው÷ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ መንገዶቿ ወብ እንዲሆኑ ዛሬ የተፈረመው የማሽነሪ ግዢ ድጋፍ አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አንጂነር ሞገስ ጥበቡ እንደገለጹት÷ ስምምነቱ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በራስ ኃይል እያከናወነ የሚገኘውን የመንገድ ሃብት ጥገና አቅም ይበልጥ በማጎልበት ውጤታማነቱን ያሳድጋል፡፡
የመንገድ ጥገና ማሽነሪዎች ግዢ ስምምነት÷ የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የመንገድ ጥገና አቅሙን በዓመት በ25 በመቶ እንደሚያሳድግ መናገራቸውንም የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
በግዢ ውል ስምምነቱ መሰረት÷ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን 81 ማሽነሪዎችን ከጃፓን መንግስት በግዢ ይረከባል፡፡
ከተማዋ ካላት አዳጊ የመንገድ መሰረተ ልማት ፍላጎት በቀጣይም የመንገድ ሽፋኑ እየሰፋ እንደሚመጣ ተመላክቷል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!