Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በፈተናዎች የማትሸነፍ ሀገር መሆኗን በየዘመኑ በማሳየት ህያው ምስክር ናት – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በፈተናዎች የማትሸነፍ ሀገር መሆኗን በየዘመኑ በማሳየት ህያው ምስክር ናት ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ተናገሩ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አመራርና ሠራተኞች የ”ኢትዮጵያ ታመሥግን” መርሐ ግብር አካሂደዋል።

በመርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በፅናት እንድታልፍ ላደረጋትና በርካታ መልካም ነገሮችን ለቸራት ፈጣሪ ምስጋና አቅርበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ቅኝ ገዥዎችን እምቢ ያለችና ሴራዎችን በመበጣጠስ ሉዓላዊነቷን ያላስደፈረች ሀገር ናት፡፡

በርካታ ውጣ ውረዶችን በማለፍ አቅም የላቸውም አይገነቡትም የተባለው ታላቁ የህዳሴ ግድብን በኢትዮጵያውያን ጥሪት በመገንባት ኃይል እንዲያመነጭ መደረጉ የአሸናፊነቷ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህ እንዲሆን ላበረታን ፈጣሪም ምስጋና ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያን በስፖርቱ መስክ ከጥንት እስከዛሬ ሰንደቅ ዓላማዋ ከኃያላኑ ተርታ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ላደረጉ አትሌቶች ምስጋና ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ድሏንና ታሪኳን ማስቀጠል የቻለች ሀገር ናት ያሉት አቶ ተፈሪ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያጋጠሙ ፈተናዎችን በኅብረ ብሔራዊ አንድነት መሻገር መቻሉን ጠቅሰዋል።

ሀገሪቱ መሪን እስከ ጦር ሜዳ ያስዘመተ የፈተና አውድ ውስጥ እንደነበረች ጠቅሰው መሪዎችና ሕዝቡ በመናበብ ሀገራቸውን ከመበታተን ስጋት ማውጣታቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ ላይ ፈተናዎችን ተሻግረን አንፃራዊ የሰላም ተስፋ ማየት ጀምረናል ያሉት ሚኒስትሩ÷ ለዚህም ፈጣሪ ሊመሠገን ይገባዋል ብለዋል።

መሪና ተመሪ ተግባብተው ለጋራ ዓላማ ከሰሩ ስኬት አይቀሬ መሆኑን ገልጸው፥ በቀጣይም በሁሉም የልማት መስኮች በአንድነት መረባረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ጫናዎች ኢትዮጵያን ለበለጠ ሰላም ለብልፅግና በምታደርገው ጉዞ ያበረቷታል እንጂ ወደኋላ አይጎትቷትም ብለዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሟትን ሴራዎችና ፈተናዎች በመቋቋም ወደፊት በመገስገስ ህያው ምስክር ሆናለች ነው ያሉት።

በዓለም መድረክ የተሠለፉ አትሌቶቻችንም ሀገራቸው ፈተናዎችን በወርቅ በብርና በነሐስ የድል ሜዳሊያዎች ታጅባ እንድታልፍ በማድረጋቸው መመስገን እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version