አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት እና አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ።
የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀኔራል አደም መሃመድ፣ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ እና የሰራዊቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሃላፊዎችም ተሳትፈዋል።
በጉብኝታቸውም በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ርብርብ እየተገነባ ያለውን የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት ተዘዋውረው መመልከታቸውን ከመከላከያ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በዚህ ወቅትም የመከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱ ህዝቦች ሰላምና ሉዓላዊነት የማስከበር ተልዕኮውን ለመወጣት በላቀ ብቃት ላይ የሚገኝ መሆኑን ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሃመድ ተናግረዋል።
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚቃጣን ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት እና አስፈላጊውን አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ህዝብና መንግስት የሰጡትን ተልዕኮ በላቀ ብቃት እየተወጣ መሆኑን የገለጹት ጀኔራል አደም፥ ሰራዊቱ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየወሩ ከደመወዙ በመቆጠብ የዜግነት ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
ጉብኝቱ መከላከያ ሰራዊቱ የህዳሴ ግድቡ የግንባታ ሂደት ያለበትን ሁኔታ በመረዳት በአሁኑ ወቅት ከተለያየ አቅጣጫ የሚነዙ አሉባልታዎችን ለመመከት ተነሳሽነት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ እንደመጣ ሁሉ ወደ ፊትም ይህንን ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
የኢፌዴሪ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው፥ አየር ሃይሉ በቀጠናው የሚቃጣን የአየር ላይ ጥቃት ለመመከት ብሎም አስፈላጊውን አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

