Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ለ2015 በጀት ከ6 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ለክልሉ ለ2015 በጀት ዓመት የሚውል 6 ቢሊየን 710 ሚሊየን 502 ሺህ 301 ብር አጽድቋል፡፡
የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂ÷ ለበጀት ዓመቱ እንዲውል ከተያዘው በጀት ውስጥ 2 ቢሊየን 516 ሚሊየን 465 ሺህ 382 ብር በክልሉ ከሚሰበሰብ ገቢ የሚሸፈን መሆኑንን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም 3 ቢሊየን 690 ሚሊየን 152 ሺህ 267 ያህሉ ከፌደራል መንግሥት በድጎማ÷ ቀሪው ደግሞ ከተለያዩ ተቋማት የውስጥ ገቢ፣ ከዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያ እና ከውጪ ከሚገኝ ዕርዳታ እንደሚሸፈን አብራርተዋል፡፡
በምክር ቤቱ ከጸደቀው አጠቃላይ በጀት ውስጥ 256 ሚሊየን 200 ሺህ ብር የሚሆነው ለዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያ እንደሚውል ተመላክቷል፡፡
በክልሉ በጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም፣ የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለማልማትና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል ትኩረት ሊሰጥ ይባል መባሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልሉ የሚካሄደው የመልሶ ማቋቋም ሥራ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ÷ የገቢ መሰብሰቢያ አማራጮችን በማስፋት በዕቅድ ከተያዘው በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደሚጠበቅ የምክር ቤት አባላቱ አሳስበዋል፡፡

 

የክልሉ ምክርቤት 14ኛ መደበኛ ጉባዔ የክልሉን ሚዲያ የቦርድ አባላት እና ሚዲያውን ለማቋቋም የወጣውን ጨምሮ የተለያዩ የማሻሻያ አዋጆችን በማጽደቅ ተጠናቋል፡፡

በዚህም ምክር ቤቱ÷ የክልሉን የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ለማቋቋሚያ አዋጅን መልሶ ለማሻሻል የወጣ ረቂቅ አዋጅ፣ የክልሉን የማረሚያ ቤት ኮሚሽን እንደገና ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ለመመዝገብና ለማስተዳደር የወጣ ረቂቅ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version