አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ክልሎች ካርታን በዛሬው እለት ይፋ አደረገ።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች የተካፈሉበት፥ የምርጫ ክልሎች ይፋ የሚደረጉበት የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የምርጫ ክልል ምነንነትና አከላለል እንዲሁም የከዚህ በፊት አከላለልና ህጋዊ ማዕቀፍን አስመልክቶ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በውይይት መድረኩ ላይ ለመጭው ጠቅላላ ምርጫ የተዘጋጀው የምርጫ ክልሎች ካርታ ይፋ ሆኗል።
በዚህ መሰረት 547 የምርጫ ክልሎች ይፋ ተደርገዋል።
በዚህም መሰረት ትግራይ 38፣ አፋር 8፣ አማራ 138፣ ኦሮሚያ 178፣ ሶማሌ 23፣ ቤኒሻንጉል 9፣ ደቡብ 123፣ ጋምቤላ 3፣ ሀረሪ 2፣ ድሬዳዋ 2 እንዲሁም አዲስ አበባ 23 ለፌደራል ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ይኖራቸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፥ ለ2012 አጠቃላይ ምርጫ የምርጫ ክልሎች ካርታን በተመለከተ የተደረገው ዝግጅትን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል።
በገለፃቸውም ቦርዱ 547 የምርጫ ክልሎች መኖራቸውን ከመግለፅ ባለፈ በካርታ ይፋ የምርጫ ክልል ኖሮት እንደማያውቅ እና ይህ የመጀመሪያው የምርጫ ክልሎችን የሚያሳይ ካርታ እንደሆነ ተናግረዋል።
ያሉትን የምርጫ ክልሎች በካርታ ከማሳየት ውጪ ቦርዱ አዲስ የምርጫ ክልል ዝግጅት እንዳላደረገም አሳውቀዋል።
በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ ተሳታፊዎች ይፋ የተደረገውን የምርጫ ክልል ካርታዎችን የተመለከቱ ሲሆን ጥያቄዎንም አቅርበው በቦርዱ በኩል ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል።
በሀብታሙ ተክለስላሴ እና በአወል አበራ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

