አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓባይ እንደተለመደው በድል የሚገባውን አስቀርቶ፥ የሚገባቸውን እየሰጠ መጓዝ መጀመሩን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ÷ በዛሬው ዕለት ሦስተኛው ዙር የታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት መጠናቀቁን አብስረዋል፡፡
በማብሰሪያ ንግግራቸው÷ “ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሁም በእዚህ ሥፍራ በዕውቀትና በጉልበት የተሳተፋችሁ የኢትዮጵያ ድንቅ ልጆች፥ ከዚህም ባሻገር የዚህን ፕሮጀክት ጠቃሚነት ተገንዝባችሁ ኢትዮጵያን በሀሳብ፣ በተለያየ መንገድ ስትረዱ የቆያችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች በሙሉ ዛሬ በዚህ ሥፍራ ሦስተኛው ዙር የውኃ ሙሌት መጠናቀቁን ሳበስራችሁ በታላቅ ደስታ ነው” ብለዋል፡፡
ይህ ክንውን አምና ከነበረው ጋር ለማነጻፀርም አምና በመሀከል ውኃ የሚፈስበት ቦታ 575 ሜትር እንደነበር አውስተው፥ ዘንድሮ ተጨማሪ 25 ሜት ከፍ በማድረግ 600 ሜትር ላይ የውኃው ፍሰት መታየቱን ገልጸዋል፡፡
ግራና ቀኝ አምና 585 ሜትር ነበር፤ ዘንድሮ 611 ሜትር በመድረስ በከፍተኛ ደረጃ ውኃ የመያዝ እና ኃይል የማመንጨት አቅማችንን ከፍ አድርጎታልም ነው ያሉት።


