Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል የጀመረችው ጉዞ ሲቃኝ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በግጭቶች፣ መከራዎችና ረሃብ ስትፈተን የቆየች ሀገር ብትሆንም አሁን ላይ ግን ካለፈው ትምህርት ወስዳ ሁኔታዎቹን ወደ ዕድል መቀየር መቻሏን በኬንያ ናይሮቢ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት የሥራ ፈጠራ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ቢታንጌ ንዴሞ ይገልፃሉ።

በኬንያው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ላይ በሚያወጧቸው ምሁራዊ ትንታኔዎች የሚታወቁት ፕሮፌሰሩ፥ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ በድኅነት የዓለምን ትኩረት የሳበች ሀገር ሆና የቆየች መሆኗን በፅሑፋቸው አንስተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ቢታንጌ ንዴሞ፥ ኢትዮጵያን ፈተናዎቿ አጠንክረዋት እና ወደ ዕድል ቀይራ አሁን ላይ በቀጠናው በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ ኢኮኖሚ መገንባት እንደቻለች ፅፈዋል።

ፕሮፌሰሩ በፅሁፋቸው፥ በሩሲያ – ዩክሬን ግጭት አፍሪካ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ስትሰቃይ ኢትዮጵያ ግን በስንዴ እህል ራሷን እንደቻለች እና የምግብ ዋስትናዋን በማረጋገጥ ግብርናውን ከንግድ ጋር አስተሳስራ ማስኬድ የሚያስችላትን ስትራቴጂ መቅረጿን አውስተዋል፡፡

ለአብነትም ይላሉ ፕሮፌሰር ቢታንጌ ንዴሞ ÷ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ካመረተችው 1 ነጥብ 42 ሚሊየን ቶን የስንዴ እህል ዘንድሮ በከፍተኛ ደረጃ አሳድጋ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን ስንዴ መሰብሰብ እንደቻለች በአድናቆት ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ቀዳሚ ስንዴ አምራች መሆኗንም ጸሓፊው ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2023 በምግብ እህል ራሷን ለመቻል እና ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምርቱን ለመላክም ዕቅድ እንዳላት አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት መሥኖን በመጠቀም የኩታ ገጠም እርሻ እውን ማድረጉ ደግሞ የሀገሪቷን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ማረጋገጥ ያስረዳሉ።

ፕሮፌሰር ቢታንጌ ንዴሞ ፥ አሁን ላይ በአፍሪካ የሚስተዋለው የምግብ እህል እጥረት የጂኦ ፖለቲካ ጉዳይ እንደሆነ በጽሑፋቸው አንስተዋል።

የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ከሩሲያው አቻቸው ፑቲን ጋር ሲገናኙ የሩሲያ-ዩክሬንን ግጭት ለአፍሪካ መልካም ያልሆነ ዜና ነው ማለታቸውም አሳዛኝ እና አፍሪካ የራሷን ምግብ ማምረት ያልቻለች አኅጉር አድርጎ ያሳየ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ከአፍሪካ አኅጉር ውጪ ያሉ መሪዎች የማኪ ሳልን ንግግር ለፖለቲካ ፍጆታቸው እንደተጠቀሙበት እና በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት አፍሪካ ረሃብ ታስተናግዳለች እንዲሉ እና ዜናውን እንዲቀባበሉ እንዳደረጋቸውተናግረዋል፡፡

የተራቡ አፍሪካውያን ሕጻናትን እና ያዘኑ እናቶቻቸውን የሚያሳዩ ምስሎች በመላው ዓለም የቴሌቪዥን መስኮት በሥፋት እንዲታዩ መደረጋቸው ለአፍሪካ አሳዛኝ ትዕይንት መሆኑንም ፕሮፌሰር ቢታንጌ ንዴሞ ይገልፃሉ።

የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ተሞክሮ በእጅጉ መማርና በምግብ አቅርቦት በኩል ካደጉ ሀገራት ወቅታዊ ሁኔታ ተፅዕኖ ሥር ነጻ በመውጣት በምግብ ራሳቸውን መቻል እንዳለባቸው መልዕክታቸውን ቢዝነስ ዴይሊ አፍሪካ ላይ አስፍረዋል።

 

Exit mobile version