Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለህወሃት የጦር መሳሪያ ጭኖ የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሶ የገባ አውሮፕላን መምታቱን መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን መዳከም የሚፈልጉና ለዚሁም ለዘመናት የሚንቀሳቀሱ ህወሃትን በመደገፍ ላይ የሚገኙ ታሪካዊ ጠላቶች ንብረት እንደሆነ የሚታመን አውሮፕላን ለሽብር ቡድኑ የጦር መሳሪያ ጭኖ በሱዳን አልፎ የአየር ክልላችንን ጥሶ ሲገባ በጀግናው አየር ኃይል ተመትቶ ወድቋል ሲል የሀገር መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።

ሠራዊቱ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ዝግጁ መሆኑም ተገልጿል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ህብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ላለፉት በርካታ ወራት ከፍተኛ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው አሸባሪው ህወሃት ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ኃይሉን ለውጊያ ሲያስጠጋ ነበር።

በየጊዜውም ተኩስ እየከፈተ የሀገር መከላከያን ሲተነኩስ መቆየቱንም ነው ያነሱት።

ቡድኑ መንግስት የዘረጋውን የሰላም አማራጭ ከቁብ ሳይቆጥርና የሰላም ሂደቱ ቴክኒካሊ ፈርሷል ብሎ መግለጫ ባወጣ ማግስት ትናንት ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ሌሊት 11 ሰዓት ላይ በቆቦ ግራና ቀኝ ባሉ አካባቢዎች፣ በዞብል ተራራ፣ በቢሶበርና በወትወት ውጊያ መክፈቱን ገልጸዋል።

በዚህም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ማፍረሱን ጠቅሰው፤ የሽብር ቡድኑ እየላከ ያለው ጀሌ በሀገር መከላከያ ሠራዊትና በጸጥታ ሃይልች እየተለበለበ ነው ብለዋል።

ሜጀር ጀኔራሉ አክለውም በሱዳን አድርጎ የአየር ክልላችንን ጥሶ በሁመራ ሰሜናዊ ክፍል በኩል ወደ ትግራይ ሊያልፍ የነበረና ለሽብር ቡድኑ የጦር መሳሪያ ሊያቀበል የነበረ አውፕላንም በጀግናው አየር ሃይል ምሽት ወደ ሶስት ሰዓት ተኩል አካባቢ ተመትቶ መውደቁን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስደፈር የሽብር ቡድኑን እየጋለቡ ያሉ ሃይሎች ቢኖሩም የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ኢትዮጵያውያነ ሀገራቸውን ለማስክበር በተጠንቀቅ ላይ ምህናቸውን ጠቅሰዋል በቀጣይም የሽብር ቡድን ሀገር የማፍረስ ህልሙን ትቶ ወደ ሰላማዊ መፍትሔ ካልመጣ እስከመጨረሻው ርምጃ ለመውሰዱ ሙሉ ዝግጅተ መደረጉን ጠቅሰዋል።

አሁን የመከላከል ርምጃ እየተወሰደ ሲሆን በቀጣይም የማጥቃት ርምጃዎች እንደሚኖሩ ነው የጠቀሱት።

Exit mobile version