አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የህወሓትን ፀብ አጫሪ ድርጊት እንዲያወግዝ ጥሪ አቀረበ።
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ህወሓት የሰላም አማራጮችን በመተው በትናንትናው እለት ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።
ቡድኑ የኢትዮጵያ መንግስት ሌላ ‘’ጦርነት ጀምሯል’’ ሲል በውሸት መወንጀሉን ያነሳው መግለጫው ፥ ቡድኑ የውሸት ፕሮፓጋንዳውን በመንዛት የቀረበውን የሰላም አማራጭ አለመቀበሉንም አውስቷል።
ከዚህ ባለፈም ህወሓት የትግራይ ወጣቶችን በግዳጅ መልምሎ በማሰልጠንና በሃሰት ፕሮፓጋንዳ በመመልመል ጦርነት መክፈቱንም ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ባለፉት ወራት ቁርጠኝነት ማሳየቱን ያነሳው ሚኒስቴሩ ፥ በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት መንግስት ከመጋቢት ወር ጀምሮ የተናጠል የሰብአዊ ተኩስ ማቆም ማድረጉን አስታውሷል፡፡
በተጨማሪም መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍ ሲያቀርብ መቆየቱንም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ያነሳው፡፡
መንግስት ለትግራይ ክልል ህዝብ የሚደረገውን ሰብዓዊ ዕርዳታ በተቀላጠፈ መልኩ ለማድረስ ከማመቻቸቱም በተጨማሪ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለትን የማገገሚያ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ከተመድ የፕሮጀክት አገልግሎት ቢሮ ጋር የሶስተኛ ወገን ትግበራ ስምምነት መፈራረሙንም አስታወሷል።
ህወሓት አሁንም ቢሆን የተለመደ ሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳ መንዛቱን ቀጥሏል ያለው መግለጫው፥ ቡድኑ የፈጸመው የነዳጅ ዝርፊያም ለትግራይ ህዝብ ደህንነት ብሎም ለሰብአዊነት መርሆዎች ደንታ እንደሌለው ማሳያ መሆኑንም ጠቅሷል።
መንግስት አሁንም ቢሆን በህወሓት የጭካኔ ባህሪ እና ደንታ ቢስ አካሄድ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስ ከረጂ አካላት ጋር ተባብሮ መስራቱን እንደሚቀጥልም አጽንኦት ሰጥቷል።
ሚኒስቴሩ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ ግጭቱን ለመፍታት የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደጎን በማለት የጀመረውን ፀብ አጫሪ ድርጊት እንዲያወግዝም ጥሪውን አቅርቧል።
አያይዞም በክልሉ ህዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ስቃይና እንግልት ሃላፊነቱ ቡድኑ መሆኑን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘበው ይገባልም ነው ያለው።
አሁንም ቢሀን መንግስት ለሀገሪቱ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የጀመረውን አካታች ሀገራዊ ምክክር አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያለው መግለጫው።
ከዚህ ባለፈም መንግስት አሁንም በትግራይ ክልል ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም እንዳለውም ነው የገለጸው።
ቡድኑ ትናንት ለፈጸመው ጥቃትና ለደረሰው ጉዳትም ሃላፊነት እንደሚወስድም አስገንዝቧል።