Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የአሸባሪው ሕወሓት ኅይሎች ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲመለሱ ጫና እንዲያደርግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ዳግም ጦርነት የቀሰቀሱ የአሸባሪው ሕወሓት ኅይሎች ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲመለሱ ጫና እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠየቀ።

አንዳንድ የውጪ ኃይሎች የሽብር ቡድኑን በመደገፍ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ከሚያደርጉት ጣልቃገብነት እጃቸውን በመሰብሰብ የሰላም መንገድን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርቧል።

53 ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ቆሞ ሰላማዊ አማራጮች እንዲቀጥሉ ሲል የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ መብርሃቱ አለሙ እንደገለጹት÷ ለረጅም ዘመን በዘለቀ ጦርነት ስልጣኔና ዕድገቷ የተገታው ኢትዮጵያ አሁንም ከጦርነት አዙሪት አልወጣችም።

አውዳሚ ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ የህዝብ ጽኑ ፍላጎት እንደነበርም ተናግረዋል።

የጦርነቱን ተጎጂዎች መልሶ ለማቋቋምና መሰረተ ልማት መልሶ ለመገንባት መጠነ ሰፊ ስራዎች ቢከናወኑም ከጉዳቱ ስፋትና ክብደት አንጻር በዘላቂነት መልሶ የማቋቋም ስራው የሚፈለገውን ያክል አለመሆኑን ገልጸዋል።

ሰላማዊ አማራጩ እያለ በወርሃ ነሐሴ በአሸባሪው ሕወሓት ኅይሎች በተከፈተው ጥቃት ሳቢያ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ምክር ቤቱን ያሳዘነ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ የሚበጀው ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት መሆኑን ጠቅሰው÷ አሁንም ቢሆን በሰላማዊ ውይይት፣ ምክክርና መግባባት ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

ምክር ቤቱ ባወጣው ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ÷ ጥቃቱን የጀመሩት የአሸባሪው ሕወሓት ኃይሎች መንግስት በወሰደው የተኩስ አቁም እርምጃ መሰረት ወደ ሠላም አማራጭ እንዲመለሱ ጠይቋል።

አሸባሪው ሕወሓት ለትግራይ ሕዝብ ሠብዓዊ ዕርዳታ የቀረበን ከግማሽ ሚሊየን ሊትር በላይ ነዳጅ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም መዝረፉ የትግራይን ህዝብ ለችግር የሚዳርግ ነውረኛ ተግባር መሆኑን ጠቅሶ አውግዟል።

መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የመጠበቅ ኅላፊነት ስላለው በቅርቡ የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሶ በገባ የጠላት አውሮፕላን ላይ የተወሰደውን እርምጃ ምክር ቤቱ ማድነቁን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version