Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲስ ወግ “ፈተና፣ ድል፣ ተስፋ” በሚል ርዕስ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2014 የመጨረሻው አዲስ ወግ ተካሄደ።

መድረኩ “ፈተና፣ ድል፣ ተስፋ” በሚል ርዕስ 2014ን በመቃኘት ነው የተካሄደው፡፡

የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እንዲሁም የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊዎች ናቸው።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ከተሠሩ የለውጥ እርምጃዎች የተነሳ የጸጥታ ተቋማት የሀገርን ሰላም ለማስከበርና ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ፣ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚያስችል አቋም ላይ ይገኛሉ።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው ፥ የሃሳብ ብዝሀነትና በሀገር ግንባታ ላይ አብሮ መሥራት ዴሞክራሲያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ መሆኑ በጋራ የሀገርን ሀብት ለማልማት እንደሚያስችል ጠቅሰው፥ የተለያየ አመለካከት ሲኖር የሀሳብ ጥራት እንዲገኝ ያስችላል ፤ አካታችነት የሚያስፈልገው ለዚሁ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

የፕላን እና ልማት ኮሚሽን ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ ፥ በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች መካከል ኢኮኖሚው እድገት ማሳየቱን አንስተዋል።

አያይዘውም ከውጪ ምንዛሬ፣ ከማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች፣ ከገቢ፣ የብድር አቅርቦትና አመላለሥ፣ ከሥራ ዕድል ማመቻቸት አኳያ ጥሩ አፈጻጸም መመዝገቡንም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ግብርና፣ አረንጓዴ ዐሻራ፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ ተጨባጭ ዕድገት ከታየባቸው መስኮች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

Exit mobile version