አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ለሽብር ተግባር ሲዘጋጁ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ።
ተጠርጣሪዎቹ በሃይማኖት ሽፋን የምዕመናን ማቆያ በሚል በቦሌ ቡልቡላ ባዘጋጁት ቤት ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን አደራጅተው ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጡ የነበሩ እና ከሃይማኖት አስተምህሮ ባፈነገጠ መልኩ የመሳሪያ ልምምድ በሚያደርጉበት ወቅት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ነው ያስታወቀው።
አራት መደበቂያ ዋሻዎችን ቆፍረው ለጥፋት ተግባር ይጠቀሙበት እንደነበር እና በሌላቸው ሥልጣን ጥፋተኛ የሚሏቸውን ግለሰቦች የማሰሪያ ቦታ አዘጋጅተው ያለ አግባብ ሲያስሩ እንደነበርም በተደረገው ክትትል እንደተደረሰባቸውም ነው ያነሳው።
ጳጉሜን 4 ቀን 2014 ዓ.ም የክትትል ቡድኑ ባካሄደው ዘመቻ አራት ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ከ385 ጥይት ጋር፣ 12 የክላሽ ካዝና፣ አራት ሽጉጥ ከመሰል 29 ጥይት ጋር፣ ሁለት የዋሻ መቆፈሪያ ማሽን፣ ሁለት የቪዲዮ ካሜራ ከእነትራይፖድ፣ ሁለት ኮምፒውተር፣ ሁለት ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ ስድስት ሀርድ ዲስክ፣ አራት ሲዲ፣ 5 የመረጃ መያዣ (ፍላሽ)፣ አራት የግምባር መብራት፣ አራት የካሜራ ሚሞሪ፣ ሦስት ባለ ሁለት የድምፅ ማጉያ፣ 300 ዩሮ እና 390 ሺህ የኢትዮጵያ ብር በማስረጃነት ተይዟልም ብሏል።
ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሽብር ተግባር ለመፈፀም በሕገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን በማደራጀት እና ትጥቅ በማስታጠቅ የጥፋት እንቅስቃሴ ላይ እያሉ ከሕዝብ በደረሰ ጥቆማ እና ግብረ-ኃይሉ ባካሄደው ብርቱ ክትትልና ዘመቻ 31 የሽብር ቡድኑን አባላት በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል።
ስለጉዳዩ በቀጣይ ምርመራው ሲጠናቀቅ መረጃው ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ግብረ-ኃይሉ ማስታወቁን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

